አንድ ቤዚን፣ አንድ ሪፖርት ፣ አንድ በጀት የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ፕሮግራም ዓላማን እውን ለማድረግ የኔዘርላንድ መንግስት የ 2.7 ቢሊየን ብር ድጋፍ አደረገ፡፡
ታህሳስ 11/2016ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአንድ ቤዚን፣ አንድ ሪፖርት፣ አንድ በጀት የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ፕሮግራም ዓላማን እውን ለማድረግ የሚያስችለውን የ 2.7 ቢሊየን ብር ድጋፍ ከኔዘርላንድ መንግስት አገኘ፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር አብርሃ አዱኛ ፕሮግራሙ በሀገሪቱ ያሉ ተፋሰሶችን መሰረት ያደረገ እቅድ ተዘጋጅቶ፤ በተፋሰሱ ውስጥ የሚገኙ ውሃን መሰረት አድርገው የሚሳተፉ ሴክተሮችን ከፌደራል አስከ ቀበሌ ያለውን መዋቅር በመጠቀም በተቀናጀ መልኩ የውሃ ሀብት ስርዓቱን ለማዘመን የሚሰራ ነው ብለዋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ፕሮግራሙን ቀርጾ ወደ ስራ ለማስገባት ላለፉት ዓመታት የፖሊሲ ማሻሻያ ከማድረግ ጀምሮ የተለያዩ አካላትን በማወያየት ፣ በመንግስት የተፈጠረውን አዲስ አደረጃጀት በመጠቀም እያንዳንዱ በተፋሰሱ ያሉ ጽ/ቤቶች የራሳቸው የቤዚን ፕላን እንዲኖራቸው በማድረግ ሰፊ ስራ ሲሰራ ቆይቷል የሚሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው፤ የዚህ ፕሮግራም ዋና ዓላማም ውሃን የመጠቀምና ምርታማ የማድረግ፣ የአቅም ግንባታ፣ የውሃ አጠቃቀም ማእቀፍ ማዘጋጀት ፣ ተቋምን የማጠናከር ፣ አጠቃላይ በውሃ ሀብት ላይ ያለውን የውሃ ብክለትና ብክነት የመቆጣጠር እንዲሁም የውሃ አካላት ዳርቻን የመጠበቅ ስራዎችን በሚገባ ማከናወን ነው ብለዋል፡፡
ፕሮግራሙ በ5ዓመት የጊዜ ገደብ የሚጠናቀቅ ሲሆን ከኔዘርላንድ መንግስት የተደረገው የ2.7 ቢሊየን ብር ድጋፍ በቀጥታ የሚውለው በአባይ፣ አዋሽ ፣ ኦሞጊቤ ፣ ስምጥሸለቆ እና ተከዜ ተፋሰሶች ላይ ትኩረት ተደርጎ ለሚሰራው የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር የማስፈን ስራ ባሻገር የአየር ንረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችሉ ስራዎች የሚሰሩበት እንዲሁም ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የተፋሰስ ጽ/ቤቶችን አቅም የሚገነባበት እና አሳታፊ የሆነ ለውጥና እድገት የሚያመጣ ስራ የሚሰራበት ሲሆን፤ የዚህ ዋና አስፈጻሚ ደግሞ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር በሚገኘው የውሃና መሬት ሀብት ማዕከል ጋር በጋራ መሆኑን ነው ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው የነገሩን፡፡
ፕሮግራሙ በከፍተኛ ሁኔታ የአየር ንብረት ለውጥን በመቆጣጠር ረገድ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ፕሮግራም በሚል ናሽናል ፕሮግራም ላይ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩን የአረንጓዴ አሻራ ኢኒሸቲቭ አንድ አካል በማድረግ ለመተግበር የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች ለመስራት ያለመ ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይ ልክ እንደ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮግራም የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ፕሮግራም በሚል በሀገር አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ በርካታ አካላት የሚጠቀሙበት፣ የምርምር ተቋማትም ስራ ላይ የሚሰማሩበት፣ አንድ ቤዚን፣ አንድ በጀት፣ አንድ ሪፖርት የሚል ዓላማ እንዲኖረው ተደርጎ እየተሰራበትን ያለውን ስራ እውን የምናደርግበት ነው ብለዋል፡፡
ድጋፉ በዋናነት የኔዘርላንድ መንግስትን ቁርጠኝነት ያሳየ ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ቤዚኖች ላይ የሚሰሩት የተለያዩ ፕሮጀክቶች በአንድ ማዕከል ተጠቃለው በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩል በተከፈተው ፕሮግራም ኮርድኔሽን ቢሮ አማካኝነት የተቋሙን እቅድ ሊያሳካ በሚችል መልኩ የተቀረጸ ፕሮግራምን የሚያሳካ ድጋፍ ነው ብለዋል፡፡