ከ132 ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ሆነዋል ተባለ።
ነሃሴ 12/2017ዓ. ም (ው.ኢ.ሚ) በአረንጓዴ አየር ንብረት ፈንድ (Green Climate Fund) ፕሮጀክት ከ132 ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃ አቅርቦት መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ተምሩ ገደፋ ገለጸዋል።
የፕሮጀክቱ የመዝጊያ መርሃ ግብር ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት አቶ ታምሩ ላለፉት 5 ዓመታት የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ በዘጠኝ ክልልሎች በመጠጥ ውሃ ፣ በመስኖና በአየር ንብረት ለውጥ ሲተገበር የቆየው ፕሮጀክቱ በርካታ የማህበረሰብ ክፍሎችን በተለይም ድርቅ የሚያጠቃቸው አካባቢዎችን የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል ብለዋል።
በፕሮጀክቱ ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች ከሰዎች ቀጥሎ ለእንስሳትም ጭምር የመጠጥ ውሃ ተደራሽ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።
በ22 ወረዳዎች ያልተጠናቀቁ እና በመጠናቀቅ ላይ ያሉትን ፕሮጀክቶች ትኩረት በመስጠት ከክልል ጀምሮ እስከ ወረዳ በጀት መድቦ ማጠናቀቅ ይገባልም ብለዋል መሪ ስራ አስፈጻሚው።
የፕሮጀክቱን ማጠናቀቂያ አስመልክቶ ግልጽ የሆነ ሪፖርት በማዘጋጀት ፕሮጀክቶች ሲዘጉ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ገንዘብ ድጋፍ ላደረጉ አካላት ፣ ለመንግስት እና ለተጠቃሚው ማህበረሰብ ግልጽ የሆነ ሪፖርት ማቅረብ ተገቢ እንደሆነም ነው መሪ ስራ አስፈጻሚው የገለጹት።
የተሰሩ ሰራዎችን ቆጥረን በተረከብነው ልክ ቆጥረን የማስረከብ ሀላፊነትን በሚገባ መወጣት አለብን ያሉት መሪ ሰራ አስፈጻሚው በአምስት አመቱ የፕሮጀክቱ ቆይታ የተከናወኑ ፣ ቀሪ ሰራዎች እና በቀጣይ ምን መደረግ እንዳለበት ጭምር በሚገባ በመፈተሽ የተሰሩት ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጡ ቀሪ ስራዎችን ደግሞ በማጠናቀቅ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አደራ ብለዋል
በፕሮጀክቱ ከዲዛይን ጀምሮ በርካታ አካላት የተሳተፉ መሆኑን የገለጹት መሪ ስራ አስፈጻሚው የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉ ግሪን ክላይሜት ፈንድን ጨምር ገንዘብ ሚኒስቴር ፣ ግብርና ሚኒስቴር ፣ ከክልል ጀምሮ እስከ ወረዳ ያሉ አካላት እና የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አመራሮችና ፈጻሚ አካላት ላበረከቱት አስተዋጽኦ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስም አመስግነዋል።
የግሪን ክላይሜት ፈንድ አስተባባሪ አቶ ጌትነት ፈጠነ ባለፉት አምስት ዓመታት በፕሮጀክቱ በውሃው ሴክተር የተተገበሩ ፣ የነበሩ ጠንካራ እና ተሞክሮ የሚሆኑ ስራዎችን በዝርዝር አቅርበው አስተያየት ተሰጥቶባቸዋል።
ከሪፖርቱ ለመረዳት እንደተቻለው የGCF ፕሮጀክት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካበረከተባቸው ክልሎች የሱማሌ ክልል ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚወስድ የተጠቀሰ ሲሆን በክልሉ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ከሰዎች ባለፈ የበርካታ እንስሳትን ህይወት መታደግ እንደቻለ ማወቅ ተችሏል።
ከዚህም በተጨማሪ በፕሮጀክቱ በርካታ የአቅም ግንባታ ስራዎች የተሠሩ መሆኑም በዝርዝር ቀርቧል።
በመጨረሻም ለፕሮጀክቱ ጥሩ አፈጻጸም የእውቅና ሰርተፍኬት ተበርክቷል።