የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን የሚያግዙ ስታንዳርዶችና መመሪያዎች ለውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ተረከቡ

የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን የሚያግዙ ስታንዳርዶችና መመሪያዎች ለውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ተረከቡ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 4/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) — ለውጤታማ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር (IWRM) ትግበራ የሚያግዙ ስታንዳርዶችና መመሪያዎች ለውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የርክክብ ሥነ-ሥርዓት ተካሄደ።

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርና በውሃና መሬት ሀብት ማዕከል በጋራ በሚተገበረው “ብራይት” (BRIGHT) ፕሮጀክት አማካኝነት የተዘጋጁት ሰነዶች ለሚኒስቴሩ በካፒታል ሆቴል በተካሄደው መድረክ ላይ ተረክበዋል።

በሥነ-ሥርዓቱ የውሃና መሬት ሀብት ማዕከል ዋና ማናጀር ዶክተር ጌቴ ዘለቀ የመክፈቻ ንግግር አድርገው፣ ሰነዶቹን በማዘጋጀት ሚኒስቴሩና ማዕከሉ በጋራ ያከናወኗቸውን ሥራዎች አስመልክተው ለተሳታፊዎች ገለጻ አድርገዋል።

በውሃና መሬት ሀብት ማዕከል የብራይት ፕሮጀክት ማናጀር ዶክተር ማማሩ አያሌው በበኩላቸው የተዘጋጁትን ስታንዳርዶችና መመሪያዎች ዋና ዋና ይዘቶች፣ የዝግጅት ስልቶችና ሂደቶች ለተሳታፊዎች አብራርተዋል።

ለሚኒስቴሩ የተረከቡት ሰነዶች ከሃይድሮሎጂ፣ ከተፋሰስ ዕቅድ፣ ከከርሰ ምድር ውሃ፣ ከጾታና ማህበራዊ አካታችነት እንዲሁም ከተፋሰሶች ከፍተኛ ምክር ቤት ማቋቋሚያ አዋጆች ጋር በተያያዙ የትኩረት መስኮች የተዘጋጁ የቴክኒክና የሕግ ማዕቀፎችን ያካተቱ ናቸው።

በኢትዮጵያ የኔዘርላንድስ ኤምባሲ ምክትል አምባሳደርና የልማት ትብብር መምሪያ ኃላፊ ሚስ ፓውላ ሺንደለር፣ ኔዘርላንድስ በኢትዮጵያ ለሚከናወኑ የውሃ ሀብት ልማትና የተቀናጀ የተፋሰስ አስተዳደር ሥራዎች የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።

ስታንዳርዶቹና መመሪያዎቹ የውሃ ሀብትን በዘላቂነት ለመጠቀምና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸውም አስረድተዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ክቡር ዶክተር ሀብታሙ ኢተፋ መድረኩን ባጠቃለሉበት ወቅት፣ ሰነዶቹ ለሚኒስቴሩ የተረከቡ ጠቃሚ የቴክኒክና የሕግ ማዕቀፎች መሆናቸውን ገልጸው የአገሪቱን የውሃ ሀብት በዘላቂነት ለመምራት፣ በዘርፉ የነበሩ የተበታተኑ አሠራሮችን በማስቀረት ወጥና የተቀናጀ አሠራር ለመፍጠር እንደሚያግዙም አስረድተዋል።

ሚኒስትሩ ሰነዶቹን በማዘጋጀት ለተሳተፉ የሚኒስቴሩ፣ የውሃና መሬት ሀብት ማዕከል፣ የብራይት ፕሮጀክት፣ የቴክኒክ ባለሙያዎችና አጋር አካላት ምስጋና አቅርበው፣ በሰነዶቹ ዝግጅት ላበረከቱት አስተዋጽኦ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም ሰነዶቹ ከዝግጅት ባሻገር ወደ ተግባር ተለውጠው ውጤት ማምጣት እንዳለባቸው አስገንዝበው፣ እስከ ክልል፣ ዞንና ወረዳ ድረስ ወርደው በተግባር እንዲውሉ አቅጣጫ ሰጥተዋል። በተጨማሪም ሰነዶቹ በሚኒስቴሩ አዘጋጅነት በሚከበሩ ታላላቅ ሁነቶች ላይ እንዲተዋወቁና በየማህበረሰቡ ቋንቋ ተተርጉመው ለሕዝብ እንዲደርሱ መመሪያ ሰጥተዋል።

ስለተቋማችን ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት

ፌስቡክ

https://www.facebook.com/share/127Jeg3ch6p/

ቴሌግራም

http://t.me/mowieethiopia

ዌብሳይት

http://mowe.gov.et

X/ትዊተር

https://x.com/mowe_ethiopia

ዩቱዩብ

https://youtube.com/@ministryofwaterandenergy-e8842?s

ቲክቶክ

tiktok.com/@mowetikto

Share this Post