በኢትዮጵያ የውሃ ዋጋ ትመና እና ዘላቂ አካታች እድገት ላይ ያተኮረ የውይይት ተካሄደ።

በኢትዮጵያ የውሃ ዋጋ ትመና እና ዘላቂ አካታች እድገት ላይ ያተኮረ የውይይት ተካሄደ።

ሰኔ18/2018ዓም(ው.ኢ.ሚ)​ በኢትዮጵያ የውሃ ዋጋ ትመና እና ዘላቂ አካታች እድገት ላይ፣ በተለይም በአዋሽ ተፋሰስ ላይ ትኩረቱን ያደረገ የምክክር መድረክ በካፒታል ሆቴል ተካሂዷል።

​በመድረኩ ላይ የተገኙት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዲኤታ ማእረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ እንደገለጹት የውሃ ሃብት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ መሰረት፣ የምግብ ዋስትና ምሰሶ እና የማህበራዊ እኩልነት መገለጫ በመሆኑ፣ ሃብቱን በአግባቡ መገምገምና ማስተዳደር ለሀገሪቱ የወደፊት ህልውና ወሳኝ ነው ብለዋል።

​የውሃ ዋጋ ትመና አስፈላጊነት የፋይናንስ መሳሪያ ብቻ ሳይሆን የውሃ አስተዳደር ስርአት ለማስያዝ እና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ የሚያስችል የመሪነት ምልክት ነውም ብለዋል።

ውሃ ተገቢው ዋጋ ሲሰጠው በብቃት እና በፍትሀዊነት ጥቅም ላይ እንደሚውል ጠቁሙዉ በተቃራኒው ዝቅተኛ ዋጋ ሲሰጠው ግን ለሀብት ብክነት፣ ለኢፍትሃዊነት እና ለግጭት መንስኤ እንደሚሆንም አቶ ሞቱማ አብራርቷዋል።

​ክቡር አቶ ሞቱማ በማከል ኢትዮጵያ ባለፉት አመታት በክትትል ስርአት፣በውሃ ተጠቃሚዎች ምዝገባ እና በተቋማዊ ግንባታ ላይ ጠንካራ ተሞክሮዎችን ብታስመዘግብም ከመሰረተ ልማት ባለፈ ጠንካራ የአስተዳደር ማዕቀፍ፣ አስተማማኝ የመረጃ ስርአት እና የተጠያቂነት አሰራርን እንደሚፈልግ ገልጸዋል ።

በመጨረሻም የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአጭር ጊዜ ፕሮጀክቶችን ወደ ረጅም ጊዜ ስርአት ለመቀየር፣ በፌዴራል እና በተፋሰስ ደረጃ ተቋማትን ለማጠናከር እንዲሁም የውሃ ዋጋ ትመናን ጨምሮ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ በማድረግ የውሃ ሃብት ለፍትሃዊ የኢኮኖሚ እድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ለማድረግ ሙሉ ቁርጠኛ መሆኑን አቶ ሞቱማ ገልጸዋል።

የውሃ እቅድ እና ክፍፍል ግምት ላይ ሳይሆን በተጨባጭ መረጃ ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት እና ተቋማት ዘላቂነትን ስለሚያረጋግጡ ከጊዜያዊ ፕሮጀክቶች ባለፈ መደበኛ ተቋማትን ማጠናከር እንደሚገባ እና አነስተኛ አርሶ አደሮችን፣ ሴቶችንና ወጣቶችን ያካተተ ልማት ማረጋገጥ እንደሚገባ ከመድረኩ ተመላክቷል።

​ የሙከራ (Pilot) ፕሮጀክቶችን ወደ ሀገራዊ ስርአት ለማሳደግ ከመጀመሪያውኑ በሀገር በቀል አቅምና በመንግስት መዋቅር ልክ መንደፍ፣ መረጃን መሰረት ያደረገ የፖሊሲ ጥበቃ ማድረግ እና ስራዎችን ከውጭ ረዳቶች ፈንድ ጥገኝነቶ አውጥቶ በብሔራዊ በጀት ውስጥ ማካተት እንደሚያስፈልግ በውይይቱ ተገልጿል።

በውይይቱ ላይ ቁልፍ የውሳኔ ሃሳቦችን ስርዓቶችን ከመንግስት የስራ ክንውኖች ጋር ማዋሃድ፣​የዘርፈ-ብዙ ቅንጅትን ማጠናከር፣​የመረጃ አስተዳደር ስርዓት መዘርጋት፣​የረጅም ጊዜ ፋይናንስ ማረጋገጥ ፣​የተቋማትን ኃላፊነት በግልጽ ማስቀመጥ እንደሆኑ በዝርዝር ተቀምጠዋል።

በውይይቱ ላይ በተነሱ ሀሳብ አስተያየቶች ምላሽ በመስጠት መድረኩን ያጠቃለሉት በውሃ ሀብት አስተዳደር ዘርፍ የተቀናጀ ውሃ ሀብት አስተዳደር መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ደበበ ደፈርሶ ናቸው።

በፕሮግራሙ ከውሀና ኢነርጂ፣ ከአዋሽ ተፋሰስ፣ ከብሉዲል፣ ከብራይት፣ ከባዘርኔት፣ ከሜታ ሜታ፣ከጣሊያን ኤምባሲ ተወካይ እና ደች ተሳትፈዋል።

Share this Post