የመንግስት አገልግሎት ሪፎርሙን ለማሳካት የብቃትና ምዘና ማዕቀፍ ስልጠና ለውሃና ኢነርጂ ዘርፍ አመራሮችና ሠራተኞች ተሰጠ።
የመንግስት አገልግሎት ሪፎርሙን ለማሳካት የብቃትና ምዘና ማዕቀፍ ስልጠና ለውሃና ኢነርጂ ዘርፍ አመራሮችና ሠራተኞች ተሰጠ።
ሰኔ 18/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ)
የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ አመራሮችና ሠራተኞች በመንግስት አገልግሎት አስተዳደር ሪፎርም የብቃትና ምዘና ማዕቀፍ እንዲሁም በመንግስት ሠራተኞች ብቃት ሥራ አመራር ይዘትና አተገባበር ላይ ያተኮረ ስልጠና እየተሰጣቸው ነው።
የስልጠና መድረኩን የከፈቱት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሥራ አመራር ዋና ሥራ አስፈጻሚና የዘርፉ የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የአብይ ኮሚቴ ጸሀፊ አቶ ኦልቀባ ባሼ ሲሆኑ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በሁለተኛው ዙር የሪፎርም ትግበራ ውስጥ ከተካተቱ ተቋማት አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ ኦልቀባ እንዳሉት፣ ከሐምሌ 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሪፎርሙ ዝግጅት የሚያስፈልጉ በርካታ የዝግጅት ሥራዎች መዘጋጀታቸውን ገልጸው ከሪፎርሙ ሰባት ዋና ዋና አምዶች መካከል አንዱ የሆነው የሠራተኞች ብቃት ምዘና ሥርዓት ተቋማዊ አፈጻጸምን ለማሻሻልና በብቃት የተደገፈ የሰው ኃይል ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን አስታውቀዋል።
ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሚሰጠው ይህ ስልጠና ተሳታፊዎች ለብቃት ፈተናው በተገቢው መልኩ እንዲዘጋጁ እና ስለ ምዘና ሂደቱ ጥልቅ ግንዛቤ እንዲያገኙ የሚያግዝ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሠራተኞች በንቃት ተሳትፈው ከስልጠናው የሚጠበቀውን ውጤት ማምጣት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
አክለውም ሪፎርሙ ወደ ተግባር ሲገባ የባለቤትነት ስሜትን በማጎልበት በተቋሙ ውስጥ የአገልግሎት ጥራትን፣ ተጠያቂነትን፣ ቅልጥፍናንና ውጤታማነትን ለማሳደግ እንደሚያስችል ገልጸዋል።
በዚህም ተቋሙ ለሀገራዊ ልማት የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ የበለጠ ለማጠናከር ይረዳል ነው ያሉት።
እንደ ዘርፉ እቅድ 45 በመቶ የሚሆኑ ሠራተኞች በብቃት ፈተናው እንዲያልፉ ታቅዶ እየተሰራ ቢሆንም፣ ሁሉም ሠራተኞች በተገቢ ዝግጅት በመሳተፍ ፈተናውን በማለፍ ብቁ የመንግስት ሠራተኛ ለመሆን ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
ስልጠናው ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በተወከሉት አቶ ተስፋዬ አጥሬ እየተሰጠ ሲሆን፣ የመንግስት ሠራተኞች ብቃት ጽንሰ-ሐሳብ፣ የብቃት ዓይነቶች፣ ምድቦች፣ የብቃት አሃዱ አመላካቾች እና የምዘና ሥርዓቱ አተገባበር በዝርዝር ቀርቧል።
በስልጠናው ወቅት ተሳታፊዎች ያነሱት ጥያቄዎችና አስተያየቶች በውይይት ተዳሰው ምላሽ የተሰጣቸው ሲሆን፣ ስልጠናው በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት ተጨማሪ ይዘቶችን በማካተት እንደሚቀጥል ታውቋል።
የብቃትና ምዘና ማዕቀፉ በዘርፉ ውስጥ ውጤት ተኮር፣ ተጠያቂና ብቁ የሰው ኃይል በመገንባት የመንግስት አገልግሎትን ለማዘመን እንዲሁም ለውጤታማ ተቋማዊ አፈጻጸም መሠረት ይጥላል።