ተፈትኖ ያለፈው የባስኬት ፈንድ ፕሮግራም
ተፈትኖ ያለፈው የባስኬት ፈንድ ፕሮግራም
ሰኔ 14/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በአነስተኛና መካከለኛ ከተሞች እ.አ.አ ከ2016 ጀምሮ ወደ ተግባር የገባው የባስኬት ፈንድ ፕሮግራም የማህበረሰብን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የዜጎችን ኑሮ የሚያሻሽል ፕሮግራም ነው።
ፕሮግራሙ የተቀረጸው የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን በከተሞች የማሳደግ ዓላማ በመያዝ ሲሆን፤ በተበታተነ መንገድ የሚገኘውን የፋይናንስ ድጋፍ በአንድ ቋት በማሰባሰብ በተደራጀ መልኩ ትርጉም ያለው ስራ ለመስራት ነው።
በዚህም የኢትዮጵያ መንግስት ከጣሊያን የልማት ትብብር ኤጀንሲ (AICS)፣ ከፈረንሳይ ልማት ድርጅት (AFD) እና ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ (EIB) ጋር በመተባበር ፕሮግራሙን እውን ለማድረግ ሲሰራ ቆይቷል።
ፕሮግራሙ ወደ ተግባር ምዕራፍ ለመሸጋገር 48 ከተሞችን በመለየት ጉዞውን ቢጀምርም የበጀት ሁኔታው ከ43 ከተሞች የማይዘል ሆነበት።
ስለዚህ አምስቱን ከተሞች በመቀነስ በ43ቱ ከተሞች ስኬታማ ውጤት ለማስመዝገብ ጉዞውን ጀመረ። በዚህም ባለፉት ዓመታት ባከናወናቸው ተግባራት 40 ከተሞችን የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ የቻለበትን ድል አስመዝግቧል።
የ40 ከተሞች የመጠጥ ውሃ ተቋማት ግንባታ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት በቅቷል። የሁለት ከተሞች ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ደግሞ ከ90 በመቶ በላይ በመድረሱ በቅርቡ እንደሚጠናቀቁ ይጠበቃል።
የአንደኛው ከተማ (ደብረማርቆስ) ፕሮጀክት በተለያየ ምክንያት የታሰበውን ያህል መጓዝ አልቻለም ነበር። ነገር ግን አሁን ላይ ፕሮጀክቱን ለማፋጠንና በአጭር ጊዜ ውስጥ ለአገልግሎት ለማብቃት ርብርብ እየተደረገ ይገኛል።
የባስኬት ፈንድ ፕሮግራም ይህንን ድል ሲያስመዘግብ ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ ሆነውለት አይደለም። በርካታ ዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ ችግሮችን በማለፍ ነው።
በተለይም በዓለም ላይ ተከስቶ የነበረው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የፕሮግራሙ ትልቅ ፈተና ሆኖ አልፏል። የወረርሽኙ መከሰት ሁሉን አቀፍ ተጽዕኖ በማሳደሩ ባስኬት ፈንድ ፕሮግራምም የዚህ ተጽዕኖ ሰለባ መሆኑ አልቀረም።
በዚህ የተነሳ በፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ ከፍተኛ መጓተት አስከትሎ ነበር።
ሌላው ፕሮግራሙን የፈተነው ጉዳይ የዓለም ዋጋ አለመረጋጋት ሲሆን፤ ይህም የግብዓት አቅርቦት ላይ የፈጠረው ጫና ፕሮግራሙ በታቀደው ልክ እንዳይጓዝ አድርጓል።
እነዚህ ግዙፍ ፈተናዎች እና ሌሎች ችግሮች በፕሮግራሙ ጉዞ ላይ እንቅፋት ሆነው ቢያልፉም ዛሬ ላይ ለስኬት መብቃት ተችሏል።
ይህ ውጤት የመጣው በተቀናጀ አሰራር፣ በአመራር ቁርጠኝነት እና በባለሙያው ትጋት ነው።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ክልሎች፣ አጋሮች እና ፕሮግራሙ የሚተገበርባቸው ከተሞች ማህበረሰብ ተቀናጅተውና ተናበው መስራታቸው ለውጤቱ መምጣት የላቀ አስተዋጽኦ ነበረው።
የሚኒስቴሩ አመራሮች ፕሮግራሙን በቅርበት በመከታተል አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጋቸው፣ ክልሎች የሚጠበቅባቸውን መወጣታቸው፣ አጋሮች ከገንዘብ ባለፈ የቴክኒክ ድጋፍ መስጠታቸው እንዲሁም የማህበረሰቡ የቅርብ ድጋፍ የባስኬት ፈንድ ፕሮግራም ፈተናዎችን እንዲሻገር አድርገዋል።
በዚህ ረገድ አማካሪዎች እና ኮንትራክተሮችም የማይናቅ አስተዋጽኦ ነበራቸው።
የ40 ከተሞችን የመጠጥ ውሃ ተቋማት ለአገልግሎት ያበቃው የባስኬት ፈንድ ፕሮግራም ባለፈው አርብ በአዳማ ከተማ ባለድርሻዎች በተገኙበት የማጠቃለያ ዓውደ ጥናት አካሂዷል።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ በዓውደ ጥናቱ መክፈቻ ላይ እንዳሉት፤ ፕሮግራሙ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን አሳድጓል።
ፕሮግራሙን ስንጀምር የጋራ ራዕያችን ለማሳካት በፍጥነት በማደግ ላይ ለሚገኙ አነስተኛና መካከለኛ ከተሞች ዘላቂ የውሃ እና የንፅህና አጠባበቅ ስርዓት ለመገንባት ያለመ ነበር ብለዋል።
ከ6.7 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተተገበረው ይህ ፕሮግራም ከ2.1 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
ፕሮግራሙ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት መብቃት በህብረተሰቡ ዘንድ ደስታ መፍጠሩን ጠቅሰው፤ ለፕሮግራሙ እውን መሆን አስተዋጽኦ ለነበራቸው ሁሉ በሚኒስቴሩ ስም ምስጋና አቅርበዋል።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ልማት ፈንድ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ዶጊሶ ጎና በበኩላቸው፤ የመጠጥ ውሃ ተቋማቱ በዘላቂነት አገልግሎት እንዲሰጡ ህብረተሰቡ እንደግል ንብረቱ ሊጠብቃቸው ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።
በባስኬት ፈንድ ፕሮግራም ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁት ፕሮጀክቶች በዘላቂነት አገልግሎት እንዲሰጡ ዝግጅት መደረጉንም ተናግረዋል።
የውሃ ተቋማቱ በአግባቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ከጥገና ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በኩል ለባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠቱን አንስተዋል።
በተጨማሪም መለዋወጫን ጨምሮ አስፈላጊው ግብዓት መቅረቡን አመልክተዋል።