የመጠጥ ውሃ ተቋማት በዘላቂነት አገልግሎት እንዲሰጡ ህብረተሰቡ እንደግል ንብረቱ ሊንከባከብ ይገባል ተባለ።
የመጠጥ ውሃ ተቋማት በዘላቂነት አገልግሎት እንዲሰጡ ህብረተሰቡ እንደግል ንብረቱ ሊንከባከብ ይገባል ተባለ።
ሰኔ 13/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በውሃ ልማት ፈንድ በኩል የሚተገበረው የባስኬት ፈንድ ፕሮግራም የማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ ከ7 ክልል የውሃ ቢሮ ኃላፊዎች፣ የ43 ከተሞች ከንቲባዎችና የውሃ አገልግሎት ኃላፊዎች እንዲሁም ድጋፍ ያደረጉ የልማት ድርጅቶች በተገኙበት ሲካሄድ የነበረው የውይይት መድረክ ላይ የመጠጥ ውሃ ተቋማት በዘላቂነት አገልግሎት እንዲሰጡ ህብረተሰቡ እንደግል ንብረቱ ሊንከባከብ ይገባል ተባለ።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ልማት ፈንድ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ ዶጊሶ ጎና የውሃ ልማት ፈንድ ከተቋቋመ 23 ዓመታት ቢሆነውም በረጅም ጊዜ ብድርና በአነስተኛ ወለድ የተገኘ ሀብትን በማስተባበር በውሃ ልማት ዘርፍ በርካታ ስራዎች ሲሰሩ እንደነበር አስታውቀዋል።
አቶ ዶጊሶ አክለውም መድረኩ የውሃ መሰረተ ልማት ፕሮጄክቶችን እንዴት ማስተዳደር እንዳለብንና በግንባታው ሂደት ልምድ የቀሰምንበት በመሆኑ መልካም ተሞክሮዎቻችንን ማስፋት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የተጠናቀቁትን ፕሮጀክቶች ወደየከተማው የውሃ አገልግሎት ተቋማት አስተላልፈናል ያሉት አቶ ዶጊሶ የጋራ ኃላፊነታችን የሆኑትን የውሃ ተቋማት የሚፈለገውን ገቢ እንዲያስገኙ ለማድረግ ከጥገና ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በኩል ለባለሞያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና ሲሰጥ እንደነበርና ለየተቋማቱም ተንቀሳቃሽ ሞተር ሳይክልን ጨምሮ የቢሮ የቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉንም አስታውሰዋል።
አቶ ዶጊሶ አያይዘውም የመጠጥ ውሃ ተቋማቶቹ በዘላቂነት አገልግሎት እንዲሰጡ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩል የአቅም ግንባታ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና በግንባታው ሂደት የነበሩ መልካም ተሞክሮዎችን በማጠናከር በቀጣይ ለሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ጥሩ ልምድ እንደተገኘበትም አክለዋል።
ተሳታፊዎችም ለውይይት በቀረበው ሰነድ ዙሪያ በሰፊው ተወያይተው፤ አቶ ዶጊሶ እና የዘርፉ ባለሙያዎች አስተያየትና ማብራሪያ ሰጥተዋል።