የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ማኔጅመንት ጋር የባዮጋዝ ማብላያ ፕሮጀክት ወቅታዊ ሁኔታና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት አካሂዷል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ማኔጅመንት ጋር የባዮጋዝ ማብላያ ፕሮጀክት ወቅታዊ ሁኔታና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ውይይት አካሂዷል።

ሰኔ12/2018 ዓም(ወ.ኢ.ሚ)​ በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ግቢ የተገነባውና በሀገሪቱ የመጀመሪያውና ትልቁ የሆነው የባዮጋዝ ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት መመረቁን ተከትሎ፣ የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሡልጣን ወሊ ከዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት ጋር በፕሮጀክቱ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ውይይት አድርገዋል።

ክቡር ሚኒስትር ዲኤታው የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ ፕላንቱ መጀመሪያ ሲገነባ የምርምር ማዕከል እንዲሆን ታሳቢ የተደረገና ከኃይል አቅርቦት ባለፈ ዋነኛ ዓላማው የተፈጥሮ አፈር ማዳበሪያውን በመጠቀም ገቢ መፍጠርና ግብርናን ምርት በማሳደግ የምግብ ሉአላዊነትን ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል።

​በውይይቱ ላይ በአሁኑ ወቅት የባዮጋዝ ፕላንቱ በአግባቡ አገልግሎት እየሰጠ እንዳልሆነ የተገመገመ ሲሆን፣ ይህንን ክፍተት ለመቅረፍ እና ቴክኒካዊ ችግሮችን ለመፍታት ለባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና መስጠት እንደሚያስፈልግም ክቡር ሚኒስትር ዲኤታው ገልጸዋል።

​ቴክኖሎጂው ለሀገሪቱ አዲስና እንደ ማሳያ የሚወሰድ በመሆኑ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ማንኛውንም አስፈላጊውን ቴክኒካዊና ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ፕሮጀክቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለውና የካርቦን ልቀትን በመቀነስ በጭስ ምክንያት የሚከሰቱ የጤና ችግሮችን ከመከላከል ባለፈ ለአየር ንብረት ለውጥ ከሚያበረክተው አስተዋጽ ያለውና በቀን 4.7 ቶን ተረፈ ምርት ለፕሮጀክቱ ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን በአመት 87,600 ኪሎ ዋት ሀይልን በመቆጠብ በአመት የሚወጣውን 12,950,000 ብር ወጭ ለማስቀረት ታሳቢ ተደርጎ የተሰራ ነዉም ተብሏል።

የወላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጉቺ ጉሌ በበኩላቸው የባዮ ጋዝ ፕላንቱ ለዩንቨርስቲውና ለአካባቢው ማህበረሰብ ያለው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን ጠቅሰው የተፈጠረውን የቴክኒክ ችግር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለመፍታት እያደረገ ያለውን ጥረት አመስግነዋል።

ፕሮጀክቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥም አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ገልጸው ፕሮጀክቱ አንዴ ወደስራ ከገባ ቀጣይ ጥገናና ሌሎች ወጪወችን በራሱ መሸፈን የሚችልና ለሌሎች ተቋማትም ማሳያ መሆን ነውም ብለዋል።

Share this Post