የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የከርሰ ምድር የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ለማካሄድ የውል ስምምነት ተፈራረመ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የከርሰ ምድር የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ለማካሄድ የውል ስምምነት ተፈራረመ።
ሰኔ 12/2018 ዓም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የከርሰ ምድር የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ለማካሄድ በዘርፉ ከተሰማሩ ኮንትራክተሮች ጋር በክቡር ሚኒስትር የስብሰባ አዳራሽ የውል ስምምነት ተፈረመ።
የውል ስምምነቱን የተፈራረሙት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚኒስቴር ዴኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ ሲሆኑ የውል ስምምነቱ የተፈረመው ከሚድሮክ ጂኦ ኤክስፕሎሬሽን ኃላ.የተ.የግ.ኩባንያ (ደቡብ ኢትዮጵያ አባያ -ጫሞ ሳይት)፣ ከአልባዴ ጠቅላላ ኮንስትራክሽንና የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ኃላ.የተ.የግ.ኩባንያ (ደቡብ ምዕራብ ጊምቦ- ጬና ሳይት) እና ከኢሲሲ ኢነርጂ ኃላ.የተ.የግ.ኩባንያ(ሲዳማ ክልል ይርጋለም ሳይት) ለሚካሄዱ የጉድጓድ ቁፋሮዎች ነው።
ፕሮጀክቶቹ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚተገበረው የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ልማት ፕሮጀክት አካል ሲሆኑ ኮንትራክተሮቹ የጉድጓድ ቁፋሮ እና ተያያዥ ስራዎችን በማካሄድ በ8ወራት ውስጥ አጠናቀው ለማስረከብ ውል የወሰዱ መሆናቸው በመድረኩ ተገልጿል።
ከነዚሁ ኮንትራክተሮች መካከልም ሁለቱ ቀደም ሲል በስራ ላይ የነበሩና ኢሲሲ ኢነርጂ የተባለው የቻይና ኩባንያ አዲስ መሆኑም የተመለከተ ሲሆን ስራውን የሚቆጣጠሩት ደግሞ ELARD እና AYJEF የተባሉት አማካሪ ድርጅቶች መሆናቸው ተመልክቷል።
ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ ተቋራጮቹ በሚኖራቸው የስራ ላይ ቆይታ በሚከናወኑ ተግባራትና ሊገጥሙ በሚችሉ መሠረታዊ ችግሮችና መፍትሔዎች ዙሪያ የተወያዩ ሲሆን አዲስ ውል ለገባው ተቋራጭም መልካም የስራ ጊዜ እንደሚሆንለት ተስፋ እንደሚያደርጉና ፕሮጀክቶቹ በውሉ መሰረት በተቀመጠው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ አሳስበዋል።
ኮንትራክተሮቹ በበኩላቸው በተሰጣቸው እድል አመስግነው በማሳሰቢያው መሠረት ተፈጻሚ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል ።
ውል ለተገባባቸው ፕሮጀክቶች የተደረገው አጠቃላይ ወጪ 1,607,457,627.67 ብር ወይም USD 10,157,500 ሲሆን በዓለም ባንክ የሚደፍ መሆኑም ተመልክቷል።