በያንጉዲ ወረዳ የአፈርና ውሃ ጥበቃና የጎርፍ አደጋ መከላከል የልማት ሥራ ለማስጀመር የባለድርሻ አካላት የማኅበረሰብ ንቅናቄ መድረክ ተካሄደ።

በያንጉዲ ወረዳ የአፈርና ውሃ ጥበቃና የጎርፍ አደጋ መከላከል የልማት ሥራ ለማስጀመር የባለድርሻ አካላት የማኅበረሰብ ንቅናቄ መድረክ ተካሄደ።

ያንጉዲ፣ ሰኔ 11/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን ለማሳለጥ በሚተገብረው የባዘርኔት ፕሮጀክት ስር አንዱ ክፍል የሆነውን የአፈርና ውሃ ጥበቃ እና የጎርፍ አደጋ መከላከል ልማት ሥራ በአፋር ክልል ያንጉዲ ወረዳ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የባለድርሻ አካላት የማኅበረሰብ ንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።

የመድረኩ ዋና ዓላማ በአዋሽ ተፋሰስ ውስጥ በሚገኘው የያንጉዲ ንዑስ ተፋሰስ ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን በመተግበር የማኅበረሰቡን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል፣ የተፈጥሮ ሀብትን መጠበቅ እና የአረንጓዴ አሻራ ተነሳሽነትን እውን ማድረግ መሆኑ ተገልጿል።

በመድረኩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የያንጉዲ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወልኦ መሐመድ ዲሙ፣ ህብረተሰቡን በማስተባበር ፕሮጀክቱን ውጤታማ ለማድረግ ከምንጊዜውም በተሻለ ሁኔታ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተፋሰስ ልማትና ጎርፍ መከላከል ዴስክ ኃላፊ አቶ በቀለ ብዙወርቅ የባዘርኔት ፕሮጀክት አንዱ ኮምፖነንት በሆነው የአፈርና ውሃ ጥበቃ እና የጎርፍ መከላከል ሥራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ተገኝተው፣ ፕሮጀክቱ በያንጉዲ ወረዳ የሚታዩ የአፈር መሸርሸር፣ የመሬት መራቆት እና የጎርፍ አደጋዎችን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

ኃላፊው እንዳስታወቁት፣ የፕሮጀክቱ ትግበራ የውሃ ሀብት ጥበቃን በማጠናከር፣ የአፈር ለምነትን በማሻሻል እና የአካባቢውን ማኅበረሰብ ከተደጋጋሚ የጎርፍ አደጋ ለመጠበቅ ጠቃሚ መሠረት እንደሚጥል ጠቁመዋል።

በተለይም በተፋሰስ አስተዳደር ላይ የተመሰረቱ ሥራዎች ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃን እንደሚያረጋግጡ ገልጸዋል።

የፕሮጀክቱ ስኬት የመንግሥት ተቋማት፣ የልማት አጋሮች እና የአካባቢውን ማኅበረሰብ የተቀናጀ ተሳትፎ እንደሚጠይቅ በመግለጽ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

በዚሁ ወቅት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የባዘርኔት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ብርሃኑ መኮነን ስለ ፕሮጀክቱ አጠቃላይ ገለጻ በማቅረብ፣ ፕሮጀክቱ በዋናነት የአርብቶ አደርና የከፊል አርብቶ አደር ማኅበረሰቦችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የተቀረፀ መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ብርሃኑ እንዳሉት፣ በጣሊያን መንግሥት የሚደገፈው ፕሮጀክት ለቀጣይ ሁለት ዓመታት ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን፣ በአምስት ዋና ዋና ኮምፖነንቶች ላይ ያተኩራል። እነዚህም የውሃና የተፋሰስ መረጃ ሥርዓትን ማሻሻል፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ማስፋፋት፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃና የጎርፍ አደጋ መከላከል፣ የአቅም ግንባታ እንዲሁም የሶላር ሚኒ ግሪድ ግንባታን ያካትታሉ ብለዋል።

በተለይም በያንጉዲ ወረዳ የሚተገበሩት የአፈርና ውሃ ጥበቃ እና የጎርፍ መከላከል ሥራዎች የመሬት መራቆትንና የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ፣ የውሃ ሀብትን በመጠበቅ እና የግጦሽ መሬቶችን በማሻሻል ለአካባቢው ልማት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ገልጸዋል።

የአዋሽ ተፋሰስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደን አብዶ በበኩላቸው፣ በያንጉዲ ወረዳ በባዘርኔት ፕሮጀክት ስር የሚተገበረው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ከአረንጓዴ አሻራ ተነሳሽነት ጋር በማስተሳሰር 500 ሺህ ችግኞችን ለመትከል በእቅድ መያዙን ገልጸዋል።

አካባቢው በርሃማና የውሃ እጥረት ያለበት በመሆኑ የዝናብ ውሃን የመያዝና የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን በስፋት ለማከናወን ዕቅድ መያዙንም ጠቁመዋል።

በመድረኩ ላይ የአዋሽ ተፋሰስ የባዘርኔት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ዮሐንስ ዘሪሁ እንደገለጹት፣ የመድረኩ ዓላማ በፕሮጀክቱ የሚተገበሩ ሥራዎች ላይ የጋራ ግንዛቤ መፍጠር፣ የባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ ማጠናከር እና ለትግበራው ምቹ ሁኔታ መፍጠር መሆኑን ገልጸዋል።

የተፋሰስ ልማት፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ እና የጎርፍ አደጋ መከላከል ሥራዎች በአንድ ተቋም ብቻ ሊሳኩ የማይችሉ በመሆናቸው የመንግሥት ተቋማት፣ የአካባቢ አመራሮች፣ የማኅበረሰብ ተወካዮች እና ሌሎች አጋር አካላት በቅንጅት እንዲሰሩ ለማነሳሳት የታለመ መሆኑንም አቶ ዮሀንስ አስረድተዋል።

በመጨረሻም ከክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ፣ ከአካባቢ ጥበቃ፣ ከግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት እንዲሁም ከመስኖና ቆላማ ልማት ቢሮዎች፣ ከዞንና ወረዳ አስተዳደሮች፣ የማኅበረሰብ ተወካዮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ሴቶችና ወጣቶች በመድረኩ ተሳትፈዋል።

Share this Post