የጨለለቅቱ ከተማ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

የጨለለቅቱ ከተማ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ። ግንቦት1/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በCRWASH ፕሮጀክት ጌዲኦ ዞን ጨለለቅቱ ከተማ በ182 ሚሊየን ብር ወጭ ያስገነባው መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምረ። በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጌዲኦ ዞን ጨለለቅ ከተማ ተገኝተው የፕሮጀክቱ መጀመርን ያበሰሩት የክልልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳደር የአርባ ምንጭ ክላስተር አስተባባሪና የስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አበባየሁ ታደሰ የጨለለቅ ህዝብ ጣፋጭ ቡና ለህብረተሰቡ እያቀረበ ያለ ጀግና በመሆኑ ለነሱ የሚመጥን የልማት ፕሮጀክት ሰርተን ለአገልግሎት ስናበቃ መንግስት ለልማት ብልጽግናም ሰው ተኮር ፓርቲ መሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል። የጨለለቅቱ ህብረተሰብ የሚያስፈልገውን የተሻለ ህይወት እንዲያገኝ የሚረዳ የእናቶችን ድካም የሚቀንስ ሴቶች ንጽህናቸውን ጠብቀው እንዲኖሩ ጊዜያቸውን ለትምህርትና ኢኮኖሚያዊያቸውን ለማሳደግ የሚረዳ እናቶችን ማእከል ያደረገ ፕሮጀክት ነው ብለዋል። ፕሮጀክቱ የከተማዋን ኢኮኖሚ የሚያነቃቃና የስራ እድልን የሚፈጥር ነውም ብለዋል። በመጨረሻም ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ ፕሮጀክቱን ለሰራው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ምስጋና በማቅረብ ህብረተሰቡ ይህን ፕሮጀክት በመጠበቅና በመንከባከብ ከተያዘለት ጊዜ በላይ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ይጠበቅበታል በማለት አሳስበዋል። በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክብር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ የከተማዋን ለዘመናት የቆዬ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፍላጎት ጥያቄ መሠረት ከ182 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ከፌደራል መንግስት በጀት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሲአር ዋሽ በኩል ተሰርቶ ለዚህ በቅቷል ብለዋል። የጨለለቅ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ውሃ ፕሮጀክት ከ49 ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸው በፕሮጀክቱ በዘላቂነት ለመጠቀም የአካባቢው ህብረተሰብ የክፍያ ስርዓቱን ተከትለው የአገልግሎት ክፍያቸውን በመክፈል መጠቀም እንዳለባቸውም ገልጸዋል። ፕሮጀክቱ ለአካባቢው ህብረተሰብ ብቻ ሳይሆን ለተቋማት ጭምር ከፍተኛ ጠቀሜታን በመስጠት የአካባቢውን ጤና እና ትምህርት ተቋማት አገልግሎት ለማሻሻል ይረዳልም ብለዋል። ክቡር ሚኒስትር ዲኤታው በማከል የጨለለቅ ከተማን የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አጠናቀን ለአገልግሎት ስናበቃ ለህብረተሰቡ በፍትሀዊነት የውሃ ክፍፍል ማድረግ ደግሞ ከውሃ አገልግሎት ይጠበቃል ብለዋል። በመጨረሻም ህብረተሰቡ ችግኝ በመትከል፣ ያሉትንም መንከባከብ፣ የአገልግሎ ክፍያውን በአግባቡ በመክፈል፣ ብክነትን በመቀነስ መጠቀም ከቻለ ተጨማሪ ፕሮጀክት መስራት ይቻላል በማለት አሳስበዋል። በመጨረሻም ፕሮጀክቱን ለተገበሩ አመራሮች፣ ባለሙያዎች፣ ኮንትራክተሮች፣ አማካሪዎች እና ለክልሉ መንግስትና ለህብረተሰቡ ክቡር ሚኒስትር ዲኤታው ምስጋና አቅርበዋል። ፕሮጀክቱ አራት ሪዘርቫየር ያለውና 36 ኪሎ ሜትር የመስመር ዝርጋታ የተሰራ ሲሆን ለ20 አመት አገልገሎት እንዲሰጥ ታሳቢ ተደርጎ የተሰራ ነው። በመርሀ ግብሩ ላይ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዲኤታን ጨምሮ የክልሉ የበላይ አመራሮች የሀገር ሽማግሌዎች ኮንትራክተሮችና የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።

Share this Post