ከግሪድ ውጪ የሆኑ ማህበረሰብን የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግና የሶላር ቴክኖሎጂን በዘላቂነት ለማስቀጠል የአቅም ግንባታ ስልጠና ወሳኝ ነው ተባለ፡፡
ሚያዝያ 30/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚተገበረው የብሔራዊ የኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ለማረጋገጥ የፀሃይ ብርሃንን ወደ ኤሌክትሪክ የሚቀይር ቴክኖሎጂ (Solar Technology) ዙሪያ ለተከታታይ ቀናት ሲሰጥ የነበረው የአቅም ግንባታ ስልጠና ማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ ከግሪድ ውጪ የሆኑ ማህበረሰብን የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግና የሶላር ቴክኖሎጂን በዘላቂነት ለማስቀጠል የአቅም ግንባታ ስልጠና ወሳኝ ነው ተባለ፡፡
በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኤሌክትሪፊኬሽንና ኢነርጂ መረጃ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ዳቢ ከግሪድ ውጪ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከመቼውም በበለጠ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ የሶላር ቴክኖሎጂን በዘላቂነት ለማስቀጠል የአቅም ግንባታ ስልጠና ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይ በሰልጣኞች የተሰጠውን አስተያየት ላይ ትኩረት በማድረግ ወደ ትግበራ ይገባል ያሉት አቶ መስፍን የሶላር ቴክኖሎጂን በዘላቂነት ለማስቀጠል የጥገና ጉዳይ ተግዳሮት በመሆኑ፤ የየክልሉን ቴክኒካል ባለሞያዎች አቅማቸውን በማሳደግ የብድር አቅርቦትንም ማመቻቸት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
አቶ መስፍን አክለውም ሰልጣኞች ስልጠና ከወሰዱ በኋላ ያገኙትን ዕውቀት ለሌሎች ባለሙያዎች የማጋራት ልምድን በማዳበር ለሶላር ቴክኖሎጂ መስፋፋት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ አሳስበው፤ ስልጠና የሰጡትን የኢትዮጵያ የኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም (ELEAP) የግሪን ኢነርጂ አማካሪን (Green Energy Consulting PLC) በሚኒስቴር መስሪያቤቱ ስም አመስግነዋል።
በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ 34 ኪሎዋት የሚያመነጨውን የሶላር ፓኔልን ዲዛይን፣ አቅርቦት እና ተከላ ላይ የተሰማራው ሊደትኮ ኃ.የተ.የግ.ማህበር የሶላር አምራች ድርጅት በአካል ጎብኝተዋል፡፡
ድርጅቱ አስተማማኝ እና ለተጠቃሚዎች ተስማሚ የሆነ የሶላር ቴክኖሎጂ መሆኑን ገለፃ ያደረጉት የድርጅቱ መሪ ስራ አስፈፃሚ ኢ/ር ደረጄ ዋለልኝ ላለፉት አስርት ዓመታት ስኬታማ ስራዎችን በመስራት የሚታወቀው ድርጅት ባለ 6 ወለል ህንፃ ላይ ሙሉ በሙሉ በሶላር ኃይል መብራትና አሳንሰርን በመጠቀም የሰራተኞች መኖሪያን ጨምሮ ለተለያዩ አገልግሎት የሚጠቀሙበት እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
ቴክኖሎጂው የኢንተርኔት ኮኔክሽንን በመጠቀም ሶላሩ ከፀሐይ ምን ያህል ኪሎዋት እንደሚያመነጭ በሞባይል መተግበሪያ ቢሮ ሆኖ መቆጣጠር ይቻላል ያሉት ኢ/ር ደረጄ አሁን ባለበት ህንፃ ላይ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አራት አመት ሲሆን ለቀጣይ እስከ 30 ዓመታት የሚያገለግል የፀኃይ ኃይል ማመንጫ ነው ብለው፤ በጉብኝቱ ወቅት በሰልጣኞች ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያም ሰጥተዋል።
በድርጅቱ የማርኬቲንግ ዳይሬክተር ወ/ሮ የምስራች ዜና በበኩላቸው ድርጅቱ እ.ኤ.አ በ1996 የተቋቋመ መሆኑን አስታውሰው፤ ፖሊሲዎችን ከማዘጋጀት ጀምሮ ከሚኒስቴር መ/ቤቱ ጋር በአደሌ ፕሮጀክት ላይ በጋራ የሚሰራ እንደሆነ፤ በቀጣይም የባዮጋዝ ማብላያን (Biogas Digester) በማቅረብ ከክልሎች ጋር በጋራ እንሰራለን ብለዋል።
ተሳታፊዎቹም ለየክልሉ ባለሞያዎች የተሰጠውን የቴክኒካል አቅም ግንባታ ስልጠና በማግኘታቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን አመስግነዋል።