የየትኛውም የልማት ስራ ዕቅድ መነሻው ተፋሰስ/ውሃ ሀብት/ መሆኑ ተገለፀ።

የየትኛውም የልማት ስራ ዕቅድ መነሻው ተፋሰስ/ውሃ ሀብት/ መሆኑ ተገለፀ። ባህርዳር # ሚያዝያ 30/2018 ዓ/ም ውኢሚ በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚተገበር በብራይት/BRIGHT/ ፕሮጀክት የተዘጋጀ የአባይ ተፋሰስ ዕቅድ ቴክኒካል ኦድት ተደርጎና ተከልሶ በተዘጋጀ ዕቅድ በአተገባበር ምዕራፍና ዕቅዱን በማዳበር ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጓል። በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚኒስቴር ዴኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስትሩ ልዩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ በውይይት መድረኩ ላይ ተገኝተው የየትኛውም የልማት ስራ ዕቅድ መነሻው ተፋሰስ/ውሃ ሀብት/ መሆኑን ተናግረዋል። የተፋሰሶች ዕቅድ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የብቻውና የግሉ ዕቅድ ሳይሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ባለቤት በመሆን በጋራ የሚያቅዱትና በቅንጅት ወደ ትግበራ ምዕራፍ የሚገቡበት ነው ብለዋል። የአባይ ተፋሰስ እንደሀገር ከፍተኛውን የውሃ አቅም የያዘ በመሆኑ ሁሉም የሚመለከተው አካል ያለውን ሀብት በጥንቃቄ ስራ ላይ በማዋል የተሻለ ውጤት በሚያመጣ መልኩ መተግበር አለበትም ብለዋል። በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ ውሃ ሀብት አስተዳደር ዋና ስራአስፈፃሚ አቶ ደበበ ደፈርሶ በተፋሰስ አስተዳደር የሚተገበሩ ስራዎች በሙሉ የአንድ ተቋም ብቻ ጎዳይ ሳይሆን የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራርንና የባለቤትነት ስሜት በመፍጠርና ተግባራዊ በማድረግ የተሻለ ውጤት የማምጣት ዓላማ ያነገበ ነው ብለዋል። በዘርፉ የተሰማሩ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የተለዩ ክፍተቶችን በመሙላት፣ ተግዳሮቶችን በመቋቋምና መፍተሄ በመስጠት እና ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል ተከልሶ ለታቀደው ዕቅድ ባለቤት በመሆን ከተፋሰሱ የሚጠበቀውን ውጤት ለማምጣት መነሳሳት ያስፈልጋል ብለዋል። በርካታ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈው ተከልሶ የተዘጋጀው የአባይ ተፋሰስ አስተዳደር ዕቅድ በታቀደው ልክ ተግባራዊ ከሆነ ከተፋሰሶች ልማት ስራ ከሚገኝ ትሩፋት የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ ባሻገር የተፋሰሶችን ተፈጥሮአዊ ጤናማነት እንዲጠበቅና ቅንጅታዊ አሰራር እንዲበረታታ ያደርጋል ብለዋል። ከዚህ ቀደም በዓባይ ተፋሰስ ትግበራ ምዕራፍ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና ክፍተቶች እንዳይደገሙ ምንስቴር መስሪያ ቤቱ የህግ ማዕቀፎችን አዘጋጅቶ ከነበረው በተለየ ሁኔታ ድጋፍና ክትትል ለማድረግና ተከታታይ የገግምገማና የውይይት መድረክ ለማካሄድ መታቀዱን አቶ ደበበ ገልፀዋል። በዘርፉ ባለሙያዎችና ምሁራን በቀረቡ ሰነዶች ላይ በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ከመድረክ ምላሽ፣ ማብራሪያና ቀጣይ የትግበራ ምዕራፍ አቅጣጫም ተቀምጧል።

Share this Post