ኢትዮጵያና አዘርባጃን በውኃና ኢነርጂ ዘርፍ የትብብር እድሎችን ለማጠናከር ተወያዩ።

ኢትዮጵያና አዘርባጃን በውኃና ኢነርጂ ዘርፍ የትብብር እድሎችን ለማጠናከር ተወያዩ። ሚያዚያ 30/2018 ዓ.ም — አዲስ አበባ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ፣ በአዘርባጃን ሪፐብሊክ ምክትል የኢኮኖሚ ሚኒስትር H.E. Elnur Aliyev የተመራና ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት የተውጣጡ 11 አባላትን ያካተተ የልዑካን ቡድን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው ውይይት አደረጉ። ውይይቱ የተካሄደው፣ በቅርቡ ክቡር የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አሕመድ በአዘርባጃን ሪፐብሊክ ባደረጉት ጉብኝት ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ክቡር ኢልሀም አሊየቭ ጋር በተደረገው ውይይት ከተስማሙባቸው ዋና ጉዳዮች መካከል የሁለቱን አገራት የኢኮኖሚ ትብብር ማጠናከር በመሆኑ ነው። በዚሁ መሠረት የአዘርባጃን የልዑካን ቡድን በውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በመገኘት፣ ኢትዮጵያና አዘርባጃን በውኃ እና ኢነርጂ ዘርፍ ሊኖራቸው በሚችሉ የልማት ትብብር እድሎች ዙሪያ ከክቡር ሚኒስትሩ ጋር ምክክር አድርገዋል። ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያ ተፈጥሮ የለገሳትን ሀብት በመጠቀም የህዝቦቿን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስና የኑሮ ደረጃን ለማሻሻል ከህብረተሰቡ እና ከልማት አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር በርካታ ስራዎችን እያከናወነች መሆኗን ገልጸዋል። እንዲሁም ሚኒስቴሩ በአዋጅ የተሰጡትን ዋና ዋና የስራ ዘርፎች ማለትም የውኃ ሀብት አስተዳደር፣ የመጠጥ ውኃና ሳኒቴሽን እና የኢነርጂ ልማት ዘርፎችን በመጥቀስ፣ በእነዚህ ዘርፎች ከአዘርባጃን ጋር በትብብር ሊሰሩ የሚችሉ በርካታ ዕድሎች እንዳሉ ለልዑካን ቡድኑ ማብራሪያ ሰጥተዋል። የአዘርባጃን ምክትል የኢኮኖሚ ሚኒስትር H.E. Elnur Aliyev በበኩላቸው፣ አዘርባጃን ጠንካራ የኢኮኖሚ አቅም ያላት ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፣ በውኃና ኢነርጂ ዘርፍ የመንግስትም ሆነ የግሉ ዘርፍ ተቋማት ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል። በተለይም በውኃ እና በታዳሽ ኃይል ልማት ዘርፍ ሁለቱ ሀገራት በጋራ ሊሰሩባቸው የሚችሉ ተጨባጭ እድሎች መኖራቸውን አመልክተዋል። በመጨረሻም፣ በተደረገው ውይይት መሠረት በቀጣይ በጋራ ለመስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መግባባት የተደረሰ ሲሆን፣ ከአዘርባጃን ወገን የቀረበውን የትብብር መግባቢያ ሰነድ ሚኒስቴሩ ከመረመረ በኋላ እንደሚፈርም ክቡር ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።

Share this Post