በዘጠኝ ከተሞች የሳኒቴሽን መሠረተ ልማት የጥናት ሪፖርት ላይ ውይይት ተካሄደ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በ24 ከተሞች እያከናወናቸው ካሉ የሳኒቴሽን መሠረተ ልማት ግንባታዎች መካከል የዘጠኝ ከተሞችን የጅማሮ ሪፖርት (Inception Report) ለመገምገምና ለማጽደቅ የሚያስችል የውይይት መድረክ አካሄደ።
ሚያዚያ29/2018ዓም(ው.ኢ.ሚ)የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሳኒቴሽን መሠረተ ልማት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኑረዲን መሀመድ እንደገለጹት ሚኒስቴሩ በ24 ከተሞች የሳኒቴሽን ጥናት እያካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የዕለቱ መድረክም በውሉ መሠረት የዘጠኝ ከተሞችን የመጀመሪያ የጥናት ሪፖርት ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ለመገምገም የታለመ ነውም ብለዋል።
አሁን የቀረበው የመጀመሪያው ሪፖርት ሲሆን፣ በቀጣይ አራት ተከታታይ ጥናቶች እንደሚከናወኑ ተገልጿል።
የባለድርሻ አካላት ድርሻ አማካሪው ድርጅት ስራውን ለመስራት ባቀደው ዘዴ (Methodology) እና የጊዜ ሰሌዳ ላይ የጋራ መግባባት መፍጠር የውይይቱ ዋና ትኩረት መሆኑን አቶ ኑረዲን ጠቁመዋል
የከተማ ሳኒቴሽን መሠረተ ልማት ጥናት ዲዛይን ግንባታ ተቆጣጣሪ አቶ ገመዳ አበራ ጥናቱ በሁለት ምድብ (Lot) ተከፍሎ በሦስት ክልሎች (አማራ፣ ኦሮሚያ እና ሶማሌ) እንደሚካሄድ የገለጹ ሲሆን ሎጥ 1፡ ዱከም፣ ሞጆ፣ ለገጣፎ እና ወሊሶ ሎጥ 2፡ ቶጎ ውጫሌ፣ ጎዴ፣ ቀብሪደሃር፣ ደብረ ማርቆስ እና ፍኖተ ሰላም መሆናቸውን አስረድተዋል።
ጥናቱን የሚያካሂደው አማካሪ ድርጅት ቾካቫቲያ አሶሼትስ (Chokhavatia Associates) ከዳይናሚክ ፕላነርስ ኃ.የተ.የግ.ማ. ጋር በሽርክና ኘው።
የከተማ አቀፍ ንፅህና ዕቅድ አዋጭነት ጥናት፣ የሰገራ ዝቃጭ እና የቆሻሻ ውሃ አስተዳደር ዝርዝር ዲዛይን የጊዜ ገደብ ጥናቱን ለማጠናቀቅ 450 ቀናት መሆኑም ተገልጿል።
ለከተማ ውሃ አገልግሎቶች ሥራው ወደ ተግባር ሲቀየር ሊያጋጥሙ የሚችሉ እንቅፋቶችን ለማስቀረት፣ የየከተሞቹ የውሃ አገልግሎት ተቋማት ትክክለኛ መረጃ በመስጠት የቅርብ ድጋፍ እና ክትትል በማድረግ ጥናቱ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ እንዲተባበሩ አሳስበዋል።
በመድረኩ ላይ ከየክልሉ የተውጣጡ የውሃና ኢነርጂ ተወካዮች እና የከተማ ውሃ አገልግሎት ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።