በሶላር ቴክኖሎጂ ከግሪድ ውጪ ለሆነው ማህበረሰብ ኤሌክትሪፊኬሽንን ለማረጋገጥ የክልልና የግሉ ዘርፍ ሚና የላቀ ነው።
ሚያዝያ 28/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚተገበረው ብሔራዊ የኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራምን ለማረጋገጥ የፀሃይ ብርሃንን ወደ ኤሌክትሪክ የሚቀይር ቴክኖሎጂ (Solar Technology) ዙሪያ የሚሰጠው የአቅም ግንባታ ስልጠና ላይ በሶላር ቴክኖሎጂ ከግሪድ ውጪ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ኤሌክትሪፊኬሽንን ለማረጋገጥ የክልልና የግሉ ዘርፍ ሚና የላቀ ነው ተባለ።
ስልጠናውን በይፋ ያስጀመሩት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኤሌክትሪፊኬሽንና ኢነርጂ መረጃ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ዳቢ ፕሮጀክቱን ለመተግበር በተደረገው የዳሰሳ ጥናት መሰረት የተዘጋጀ ስልጠና መሆኑን ጠቁመው፤ በተቀናጀ የዲዛይን አቀራረብ ለመተግበር የግሪድ መዳረሻ ቦታዎች ላይ ኤሌክትሪክን ተደራሽ ለማድረግ እና ከግሪድ ውጪ ለሆነው ማህበረሰብ በቴክኖሎጂ የታገዘ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ነው ብለዋል።
በሶላር ቴክኖሎጂ ከግሪድ ወጪ ለሆኑ ማህበረሰብ ኤሌክትሪፊኬሽንን ለማረጋገጥ የክልልና የግሉ ዘርፍ ሚና የላቀ ነው ያሉት አቶ መስፍን የአደሌ ፕሮግራም ዓላማው ሁለንተናዊና መሰረታዊ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ለሁሉም ማህበረሰብ ክፍል ማረጋገጥ ስለሆነ የሶላር ካምፓኒዎች ላይ የሚሳተፉትን የግሉን ዘርፍ በተሻለ አቅምና ቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ ያለመ ነውም ብለዋል።
አቶ መስፍን አያይዘውም ከስልጠናው በኃላ በፕሮጀክቱ አገር አቀፍ ፓሊሲዎችን ለመተግበር የሚያግዝ መሆኑን ጠቁመው፤ ስልጠናው በቴክኖሎጂ ላይ ያተኮረ ብቻ ሳይሆን የሶላር ቢዝነስን እንዴት ማስኬድ ይቻላል የሚለውንም ያካተተ በመሆኑ ሰልጣኞች በንቃት እንዲሳተፉና ተሞክሮዎችንም እንዲያጋሩ አሳስበዋል።
ለስልጠናው መሳካትም የተቋሙን የበላይ አመራር አመስግነው፤ በተሰጠው ስልጠና ዙሪያ በጋራ የሚሰራውንም የኢነርጂ አማካሪዎችን አመስግነዋል።
ስልጠናው ከግሪን ኢነርጂ አማካሪ ጋር በጋራ የሚሰጥ ሲሆን ከሁሉም ክልሎች ለተውጣጡ የኢነርጂ ባለሙያዎች እና ለሚመለከታቸው የተቋሙ ባለሙያዎች ለተከታታይ ሶስት ቀናት በአማካሪዎች እየተሰጠ ነው።