ብራይት ፕሮጀክት ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ የሚወገደውን ቆሻሻ ውሃ በማከም ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ስምምነት ፈጸመ።
ሚያዚያ 27/2018 ዓ.ም(ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሚተገበረው የብራይት (BRIGHT) ፕሮጀክት ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ የሚወጣውን ቆሻሻ ውሃ በማከም መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ስምምነት በካፒታል ሆቴል ፈጸመ።
ስምምነቱን የፈጸሙት የብራይት ፕሮጀክት ማኔጀር ዶክተር ማማሩ አያሌው ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ ጋር በጋራ በመሆን ነው።
በዚህ ፕሮጀክት ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በቆሻሻ መልክ የሚወጣውን ውሃ መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ለአካባቢ ማስዋብ ስራ እንዲያገለግል የሚያስችል ስራ ለመስራት ስምምነት ላይ ተደርሷል።
ቀደም ብሎም በዚህ ፕሮጀክት በአዲስ አበባ ከተማ በተገነባው ቂሊንጦ ኮንደሚኒየም ይህ ተግባር ተፈጻሚ የተደረገ ሲሆን በዋናነት የሚወገደው ፈሳሽ መጥፎ ሽታና ትንኝ አልባ በሆነ መንገድ ታክሞ ጥቅም ላይ እንዲውል ያስቻለ እንደነበር ተመልክቷል።
ዩኒቨርሲቲው ለዚህ ተግባር በስሩ ያሉ ተማሪዎችን ዕውቀትና አቅም በመጠቀም የውሃ ናሙና እንዲሰበሰቡ የማድረግና በጥናት እንዲለዩ የማስቻል ስትራቴጂ እንደሚጠቀምም ተጠቅሷል።
የደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ይህ ተግባር ለሃገሪቱ አረንጓዴ ልማት ጉልህ እገዛ የሚያደርግ በመሆኑ በሙሉ አቅሙ ወደ ተግባር ለመግባት ዝግጁ መሆኑን የገለጸ ሲሆን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በበኩሉ ዩኒቨርሲቲው ላደረገው ድጋፍና ስምምነት ምስጋናውን ለግሷል።