በውሃና መሬት ሃብት ማዕከል በኮምፒውተር አሰራር የታገዘ አዲስ ሞዴል ለግምገማ ቀረበ።

በውሃና መሬት ሃብት ማዕከል በኮምፒውተር አሰራር የታገዘ አዲስ ሞዴል ለግምገማ ቀረበ። ሚያዚያ 27/2018ዓ.ም(ው.ኢ.ሚ) በውሃና መሬት ሃብት ማዕከል ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የውሃ ሃብት አስተዳደርና ዘላቂ ልማት ለምግብና ለእርሻ በምስራቅ አፍሪካ ፕሮጀክት (WATDEV)በኮምፒውተር አሰራር የታገዘ አዲስ ሞዴል ለግምገማ ቀረበ። የመሬት ሃብት ማዕከል ምክትል ሃላፊና በኢትዮጵያ የዚሁ ፕሮጀክት ተወካይ የሆኑት ዶክተር ጠና አላምረው በዕለቱ በካፒታል ሆቴል ከተካሄደው ሁነት ጋር በተገናኘ እንደገለፁት እ.ኤ.አ ከ2023 ተጀምሮ ለአራት ዓመታት በሚዘልቀው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የውሃ ሃብት አስተዳደርና ዘላቂ ልማት ለምግብና ለእርሻ በምስራቅ አፍሪካ ፕሮጀክት (WATDEV)አዲስ የኮምፒውተር ሞዴል በማዘጋጀት ሞዴሉ በባለድርሻዎች እንዲገመገም በማድረግ ግብዓት ለማሰባሰብ እንዲቻል መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል። ዶ/ር ጠና አክለውም ሞዴሉ የተዘጋጀበት ዓብይ ምክንያት አስቀድሞ በሃገሪቱ በተመረጡ የገጠር አካባቢዎች ከአርሶ አደሮች ጋር የጋራ ውይይት በማካሄድ አሁን የሚጠቀሙበትን የአስተራረስ ዘዴና ስልተ ምርት በመለየት ማሻሻል የሚችሉበትን መንገድ ለመቀየስ አዳዲስ ተሞክሮዎችን እንዲተገብሩ ለማስቻል መሆኑን አስረድተዋል። በዚህ ግብዓት ላይ ተመስርቶም የተዘጋጀውን ሞዴል ለመገምገም የዛሬውን መድረክ ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኗል ብለዋል። የሞዴል አዘጋጅ ቡድኑም ከኒዘርላንድና ከጣሊያን ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም ከፊንላንድ ባለሙያዎች የተሳተፉበት መሆኑ ነው የተገለጸው። እንደ ዶክተሩ ገለጻ ይህ ሞዴል የጥምር ግብርና ስልት አካልና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችል ፣የአፈር ለምነትን በተለያዩ ዘዴዎች ለማሳደግ ጠቀሜታው የጎላ ከመሆኑ ባሻገር ለፓሊሲ አውጪዎች ትልቅ እገዛ የሚያደርግና ለገበሬው ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ እንደሚያስችል በአጽንኦት ተገልጿል ። ሞዴሉ በዋናነት ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ኬኒያ፣ ሱዳንና ግብፅ ላይ ትግበራ የሚደረግበት ሲሆን በመድረኩ የተሳተፉትም ከነዚሁ ሃገራት የተውጣጡ የውሃ ሃብት አጠቃቀምና በአፈርና ውሃ ጥበቃ የሙያ ዘርፍ የተሰማሩ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ናቸው። መርሃ ግብሩ ከሞዴሉ ጋር ቁርኝት ያላቸው ጉዳዮች እየቀረቡበት ለተከታታይ ሶስት ቀናት የሚቀጥል ሲሆን መሬት ላይ በማውረድ ሊያስተገብሩ የሚችሉ ባለሙያዎችን የአቅም መገንቢያ ስልጠና መስጠትም በዚሁ መድረክ ተፈጻሚ የሚደረግ ነው ተብሏል ። ሞዴሉ ግብዓት ከተሰጠበት በኋላ ፕሮጀክቱ ከመጠናቀቁ አስቀድሞ ወደ ትግበራ የሚገባበት መሆኑ ተጠቁሟል ።

Share this Post