ስልጠናው የትግራይ ክልልን የፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ጥያቄ በሚመልስ መልኩ ለመተግበር ያግዛል ተባለ።
ሚያዝያ 26/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከአለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ ከግሪድ ርቀው የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን የኢነርጂ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚተገብረው የአደሌ
(Access to Distributed Electricity and Lighting in Ethiopian) ፕሮጀክት የአቅም ግንባታ ስልጠና አንዱና ዋነኛው በመሆኑ በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ማጠቃለያ መርሃግብር ላይ የትግራይ ክልልን በኢነርጂ ዘርፍ የፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ጥያቄ በሚመልስ መልኩ ለመተግበር ያግዛል ተባለ።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአደሌ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ አዲስአለም መብርሃቱ የኢነርጂውን ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የአሰራር ስርዓትን ለመተግበር የፈፃሚውን አቅም መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኤሌክትሪፊኬሽንና ኢነርጂ መረጃ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ዳቢ በበኩላቸው ያለክልሎች ድጋፍና ያለግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ዕቅድን ማሳካት ስለማይቻል የክልሉ ዕገዛ ወሳኝ ነው ብለዋል።
አቶ መስፍን አክለውም ስልጠናውን ወደ ተግባር በመለወጥና አስቻይ ሁኔታዎችን በመጠቀም በክልሉ ያሉትን የኢነርጂ ፍላጎት ለማሟላት ከሚኒስቴር መስሪያቤቱ ጋር በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ እንዲሆኑ አሳስበው፤ ከተሳታፊዎች ለተነሱ አስተያየቶችና ጥያቄዎችም ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የትግራይ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ የአደሌ ፕሮጀክት አስተባባሪና ከፍተኛ የኢነርጂ ባለሙያ አቶ ካህሱ ገብረህይወት የአደሌ ፕሮጀክት ከ3 ዓመታት በፊት በክልሉ ተግባራዊ መደረጉን አስታውሰው፤ በፕሮጀክቱ አተገባበር ላይ የነበረውን የግንዛቤ ችግር የሚፈታ፤ የክልሉን የፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ጥያቄ በሚመልስ መልኩ ለመተግበር ባገኘነው ስልጠና ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ ጠንክረን እንሰራለን ብለዋል።
በክልተ አውላእሎ ወረዳ የኢነርጂ ባለሙያ ወ/ሮ ፀጋ ሀዱሽ ገበሬው የኢነርጂ ተጠቃሚ ለማድረግ የቻልነውን እየሰራን ቢሆንም ባገኘነው ስልጠና የአደሌ ፕሮጀክት ምንነት፣ አተገባበርና የስርዓተ ፆታ አካታችነት ላይ ግንዛቤ በማግኘታችን ለቀጣይ ስራችን ያግዘናል ብለዋል።