በአማራ ክልል በአዴሌ ፕሮጀክት አዘጋጅነት የተካሄደው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በክልሉ ለኢነርጂ ዘርፉ እድገት የተሰጠውን ልዩ ትኩረት በተግባር ያረጋገጠ ነው_ ተሳታፊዎች
ባህር ዳር#መጋቢት 28/2018 ዓ.ም በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በብሄራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም የአዴሌ ፕሮጀክት በባህር ዳር ከተማ ዩኒሰን ሆቴል ያዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በአማራ ክልል ለኢነርጂ ዘርፉ እድገት የተሰጠውን ልዩ ትኩረት ያረጋገጠ ነው ሲሉ ተሳታፊዎች ገለፁ።
መድረኩ የፕሮጀክቱ አተገባበር የተቃኙበት የተለያዩ ሰነዶች የቀረቡበትና ለገጠር የማህበረሰብ አባላት ተጠቃሚነት የግብይት ሰንሰለት ለመፍጠርና ፈጠራን ማበረታታት ላይ ግንዛቤ በማስጨበጥ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው።
በመድረኩ የተሳተፉት አቶ አያሌው ትዕዛዙ የሶላር ምርት አስመጪና አከፋፋይ ሲሆኑ እስካሁን በክልሉ በተለያዩ ዞኖች ከ1800 በላይ የቤተሰብ ሶላር ምርቶችን ማሰራጨት መቻላቸውን ጠቅሰው በስልጠናው በነበሩ ገለፃዎችም ከማይክሮፋይናንስ፣ከኢነርጂ ባለሙያዎችና አስተግባሪዎች ጋር ትውውቅ በማድረግ የጋራ ግንዛቤ የወሰድንበት ነው ብለዋል።
በክልሉ የውሃና ኢነርጂ ቢሮ የሶላር ባለሙያ የሆኑት አቶ ደርብ አሰፋ በበኩላቸው ቀደም ሲል በስራ ላይ ከባለድርሻ ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ስለፕሮጀክቱ ገለፃ ለማድረግ የግንዛቤ ክፍተት እንደነበረ ጠቅሰው አሁን ግን የነበሩ ብዥታዎች እንዲጠሩ ስልጠናው አግዞናል ብለዋል።
የሊደትኮ የሶላር ግብይት ሃላፊ የሆኑት የምስራች ዜና በበኩላቸው የአደሌ ፕሮጀክት በሶላር ምርት ስርጭት በሚኖረው ሂደት በርካታ ድጋፍ ሲያደርግላቸው መቆየቱንና
በዚሁ መርሐ ግብርም ግንኙነታቸውን የበለጠ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ምቹ አጋጣሚ እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል ።
በሌላ በኩል በክልሉ ማህበረሰቡን የሶላር ምርት ተጠቃሚ በማድረግ በኩል በሚኖረው ሂደት የብድር አገልግሎት በማመቻቸት በኩል ፀደይ ባንክ የጎላ ድርሻ እያበረከተ መሆኑን የጠቀሱት በክልሉ የባንኩ የሶላር ተወካይ የሆኑት ጌታቸው አንዱዓለም ሲሆኑ ከአጋር አካላት ጋር የጋራ ውይይት ለማድረግ ለተፈጠረው መድረክ ምስጋናችን የላቀ ነው ብለዋል።
አብዛኞቹ ተሳታፊዎችም የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩን ላመቻቸው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን ተጠናክሮ እንዲቀጥልና በስፋት እንዲዳረስ ቢደረግ ለዘርፉ እድገት ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው አስተያየታቸውን ለግሰዋል።