የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአዴሌ ኘሮጀክት የስራ አፈፃፀም ሂደት ከባ ለድርሻ አካላት ጋር በባህርዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
ባህር ህዳር# መጋቢት 27/2018 ዓ.ም (ው. ኢ .ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በብሄራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም የሚተገበረው የአዴሌ ኘሮጀክት የስራ ትግበራን በተመለከተ ከአማራ ክልል የዘርፉ አስፈፃሚዎች ጋር ለመመካከር በባህርዳር ከተማ ዩኒሰን ሆቴል የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተዘጋጅቷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኤሌክትሪፊኬሽንና ኢነርጂ መረጃ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ዳቢ እንደተናገሩት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የብሔራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ትግበራን የመምራትና የማስተባበር ሃላፊነት ያለበት ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ከዓለም ባንክ በተገኘ ፋይናንስ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪፊኬሽን (ELEAP) በተባለ ፕሮግራም በዋናነት ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ርቀው የሚገኙ ደንበኞችን የማገናኘት ስራ እንዲሁም በኢትዮጵያ የኤሌትሪክሲቲ ተደራሽነትና የብርሃን ስርጭትን ማስፋት (ADELE) በተባለ ፕሮጀክት ደግሞ ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ውጪ በሆኑ ቴክኖሎጂዎች የገጠሩን ማህበረሰብ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ የማድረግ ስራዎችን እየመራና እያስተባበረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ኢ/ር ዳኝነት ፈንታ በበኩላቸው የጊዮን መነሻ፣ የጣና መገኛ ወደሆነችው የባህር ዳር ከተማ እንኳን በደህና መጣችሁ በማለት ንግግራቸውን የጀመሩ ሲሆን ኃይል ለአንድ ሃገር የኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ መሆኑንና ለመሰረተ ልማት መሳለጥ የሚያበረክተውን ሁነኛ ሚና መኖሩን በዝርዝር አስገንዝበው ከዚሁ ጋር በተገናኘም መንግስት ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለፍፃሜ በማብቃቱ በልማቱ ዘርፍ የተገኘውን ሃገራዊ ጠቀሜታ አስረድተዋል።
በዚህ መሰረት የተጋበዙ የመድረኩ ተሳታፊዎች ከሚቀርቡት መርሃ ግብሮች ሰፊ ግንዛቤ በመጨበጥ በክልሉ የኢነርጂ ዘርፉን ለማሳደግ በሚሰሩ ስራዎች ወደ ተግባር መቀየር ይጠበቅባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል።
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ በኩላቸው እ.ኤ.አ 1970ዎቹ በአለማችን ከፍተኛ የኢነርጂ ቀውስ በመከሰቱ ሰበብ የሃይል አቅርቦት ከአንድ ሃገር እንቅስቃሴ ጋር ያለውን ቁርኝት ለማጥናት በርካታ ጥረቶች መደረጋቸውን አውስተው በዚ መሰረት የአንድ ሃገር የኢነርጂ ፍላጎት እድገት ባሳየ ቁጥር አመታዊ የምርትና እድገት መጠኑ አብሮ እንደሚያሻቅብ የጥናት ውጤቶች አሳይተዋል ብለዋል።
አክለውም እንደ ሃገር የተቀመጡትን የብልፅግና እንቅስቃሴዎች ዕውን ለማድረግ አስተማማኝ፣ አዋጭና ንጹህ ኢነርጂ ማቅረብ የግድ ስለሚል በዘርፉ ሰፊ ስራ መስራት አስፈልጓል ብለዋል።
በዚህ መሰረት ኢትዮጵያ በታዳሽ ኢነርጂ ከሃይድሮፓወር ከጂኦተርማል፣ ከፀሐይ ሃይል እስከ 150 ጊጋ ዋት ኢነርጂ የማመንጨት አቅም እንዳላት ተናግረው እስካሁን ድረስ ያለው የኤሌትሪክ ተደራሽነት ሽፋን ግን 63በመቶ ብቻ በመሆኑ በዘርፉ ሠፊ ስራ እንደሚጠበቅ አፅንዖት ሠተው አሳስበዋል።
በአማራ ክልልም እስከ አሁን በዘርፉ በተሰራው ስራ 25ሺህ የቤተሰብ ሶላር የተሰራጨ መሆን በቀጣይ ዓመትም ከ5ዋት እሰከ 50ዋት የማመንጨት አቅም ያላቸውን በትንሹ ወደ 45 ሺህ የቤተሰብ ሶላሮች ለማሰራጨት መታቀዱን አመልክተዋል።
አያይዘውም በመርሃ ግብሩ ላይ የሚሳተፉት በብሔራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም በሚከናወኑ ተግባራት ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ በመውሰድ ለአፈፃፀም የበኩላችንን ድርሻ መወጣት ይጠበቃልም ብለዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የውሃና ኢነርጂ ቢሮ የኢነርጂ ሃላፊዎችና የክልል፣ የዞን እና የወረዳ ሃላፊዎች እና ባለሙያዎች፣ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የተገኙ የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎችና ባለሙያዎች፣ የክልሉ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሃላፊና ባለሙያዎች እንዲሁም የሶላር አቅራቢ ድርጅቶች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል ።
መድረኩ ከዘርፉ ጋር በተገናኘ የተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተስተናገዱበት ለሁለት ቀናት የሚቆይ ይሆናል።