የገጠር የመጠጥ ውሃ አገልግሎት አቅርቦት ዘላቂ እና ምቹ እንዲሆን ለማድረግ አስቻይና ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።

የገጠር የመጠጥ ውሃ አገልግሎት አቅርቦት ዘላቂ እና ምቹ እንዲሆን ለማድረግ አስቻይና ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው።   መጋቢት 3/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የገጠር የመጠጥ ውሃ አገልግሎት አቅርቦት ዘላቂ እና ምቹ እንዲሆን ለማድረግ የሚያስችል የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው። የፕሮጀክቱ የአፍሪካ ቀንድ ዋና ሃላፊ ሚስተር ቪክተር ቫዝቄዝ ለተሳታፊዎች በበይነ መረብ በዋናነት ትኩረት አድርገው ካስተላለፉት ሃሳብ ለመገንዘብ እንደተቻለው በፕሮጀክቱ የተገነቡ የመጠጥ ውሃ ግንባታዎችን በዘላቂነት አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ህብረተሰቡ፣የግል ድርጅቶች፣መንግስትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጉልህ ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል ሲሉ መልክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡   በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ካሳሁን በየነ በበኩላቸው የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ፣ኬንያ፣ሶማሊያ፣ጂቡቲ እና ደቡብ ሱዳን ድንበር አካባቢዎች የከርሰ ምድር ውሃ ሀብትን በማልማት የመጠጥ ውሃ ችግርን ለመፍታትና የዘላቂ ልማት ስራዎችን ለመደገፍ የተቀረጸ ትልቅ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቁመው በኢትዮጵያ በ12 ክልሎች ከ110 በላይ የመጠጥ ውሃ ተቋማት ግንባታን ያካተተ መሆኑንና የጥናትና ዲዛይን ስራዎችን ከዓለም አቀፍ አማካሪዎች ጋር በመፈራረም እየተገበረ ይገኛል ሲሉም ነው የገለጹት።   አቶ ካሳሁን አክለውም በዕለቱ የገጠር የመጠጥ ውሃ አገልግሎት አቅርቦት ዘላቂ እና ምቹ እንዲሆን ለማስቻል የምክክር መድረክ መፍጠር በማስፈለጉና ከመርሃ ግብሩ በኋላም ተሳታፊዎቹ በየስራ ድርሻቸው የተግባር ዕቅድ አዘጋጅተው ለውጤቱ እንዲረባረቡ ለማስቻል ነው ብለዋል፡፡ አስተባባሪው አስከትለው የፕሮጀክቱን አጠቃላይ ቁመና የቃኘ ሰነድ ያቀረቡ ሲሆን በዋናነት የፕሮጀክቱ የውሃ አቅርቦት አካል፣በወረዳ ደረጃ የተሰጠው ሽፋን፣የገጠር መጠጥ ውሃ ለተጠቃሚዎች በማድረስ በኩል የሚያጋጥሙ ችግሮች፣አገልግሎት የማይሰጡት ምክንያቶቻቸው፣ ለፕሮጀክቱ ትግበራ የተቀረጹ ስትራቴጂዎችና የወረዳ አጋዥ ቡድኖች አቅምና የትግበራ መርሃ ግብርን ተንትነው አቅርበዋል።   ከዓለም ባንክ የተወከሉ የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች የዩኤንዲፒ የፕሮጀክቱ ተወካይ አቶ ብሩክ ተስፋዬና የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ አማኑኤል ወልደ ጻዲቅ በፕሮጀክቱ ሽፋን የተሰጣቸው አካባቢዎች ዝርዝር፣የውሃ ሽፋን አቅርቦት ሂደት፣የታሪፍ ፓሊሲው ትግበራ፣ስኬቶችና ውስንነቶች፣የተገኙ መልካም ልምዶችና ተሞክሮዎችና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች እንዲሁም ለወረዳ አጋዥ ቡድን አማካሪዎች ምክረ ሀሳቦችን ያካተቱ ሰነዶች አቅርበዋል።   የቀረቡ ሰነዶችን መነሻ በማድረግ በተሳታፊዎቹ ዘንድ ከፕሮጀክቱ ጋር የተገናኙ መሰረታዊ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የተሰነዘሩ ሲሆን በአዎያዮቹ ዶ/ር ከበደ ገርባ /በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የፕሮጀክቱ ምክትል አስተባባሪ ፣በአቶ ካሳሁን በየነ፣በአቶ ብሩክ ተስፋዬና በአቶ አማኑኤል ወልደ ጻዲቅ አማካኝነት ሰፋ ያለ ማብራሪያና ምላሽ ተሰቶባቸዋል፡፡   በመርሃ ግብሩ ላይ ከ12 ክልሎች ከ55 የፕሮጀክቱ ወረዳዎች የተጋበዙ አስፈጻሚዎች፣የፕሮጀክቱ አማካሪዎች የዓለም ባንክ የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች እና ሌሎች አስተግባሪዎች የተሳተፉበት ሲሆን ሌሎች ተያያዥ አጀንዳዎች እየተካሄዱበት ለሁለት ቀናት የሚቆይ ይሆናል::

Share this Post