ክቡር ሚኒስትሩ የድሬዳዋ ከተማ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ፣ ማጣሪያና ማስወገጃ ፕሮጀክት ግንባታን አስጀመሩ፡፡

ክቡር ሚኒስትሩ የድሬዳዋ ከተማ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ፣ ማጣሪያና ማስወገጃ ፕሮጀክት ግንባታን አስጀመሩ፡፡   የካቲት 09/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በድሬዳዋ ከተማ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ፣ ማጣሪያና ማስወገጃ የፕሮጀክት ግንባታን አስጀመሩ፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ በመርሀግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት ከተሞቻችን እያደጉ ቢሆንም በከተማ ስታንዳርድ ልክ ማሟላት የሚገባቸውን የከተማ ጥራትና ውበት ሳያገኙ ቆይተው፤ ዜጎችን ለተለያዩ በሽታዎች ተጋላጭ ሆነውና ከተሞቻችን የቱሪስት መስህብ መሆን ሲገባቸው ለብዙ ችግሮች ተጋላጭ ሆነው መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡   በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አቅጣጫ የቱሪስት መስህብ ለሆኑ ለ5 ከተሞች ዕድሉ ከተሰጣቸው መካከል አንዱ የድሬዳዋ መሆኑን የገለፁት ክብር ሚኒስትሩ ከ1.3 ቢሊዮን ብር በላይ ከአለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የሚተገበረውና ትልቅ ፋይዳ ያለው ይህ ፕሮጀክት ዋናው ዓላማ በከተማዋ ያለውን ፍሳሽ ቆሻሻ በዘመናዊ መንገድ ማስወገድ ሲሆን ለአካባቢው ወጣቶችም የስራ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ አያይዘውም ድሬዳዋ ከተማ ቱሪስቶች የሚንቀሳቀሱበት፣ ለኑሮ ምቹ እንዲሆንና ሰዎች ወደውና ፈቅደው የሚመጡባት ከተማ እንድትሆን፣ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ዘላቂ በሆነ መንገድ በመስራት የአካባቢው ቆሻሻ በአግባቡ ተወግዶ ከተማዋ የምትናፈቅ ድሬ እንድትሆን የአካባቢው ነዋሪዎችም ሆነ ወጣቶች ለፕሮጀክቱ አሻራችሁን በማኖር ትልቅ ድጋፍ ልታደርጉ ይገባልም ብለዋል፡፡   በተለያየ አግባብ መሬታቸውንም ከካሳ ነፃ አድርገው ለልማቱ እንዲውል የተደረገበትንም አግባብ የከተማውን ከንቲባ አመስግነው፤ በቀጣይ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ማገዝ የሚገባውንም ለማገዝ ከከተማው ከንቲባ ጎን መሆናቸውንም ክቡር ሚኒስትሩ አክለዋል፡፡ የድሬደዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክብር አቶ ከድር ጁሃር የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት የህዝባችንን ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የውሃና ሳኒቴሽን መሰረተ ልማት ግንባታ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓታችንን በላቀ ደረጃ የሚያሻሽለው ፕሮጀክት በከተማ አስተዳደሩ የሚታየውን የመፀዳጃ አገልግሎት ችግርን ማቃለል የሚችል ሲሆን ድሬዳዋን ዘመናዊ ከተማ ለማድረግና ሁለንተናዊ የብልፅግና ጉዞ ለማረጋገጥ የጀመርነውን ግስጋሴ ለማፋጠን የበኩላችንን እስተዋፅኦ እናደርጋለን ብለዋል።   ለፕሮጀክቱ ግንባታ ከ13 ሄክታር በላይ የግንባታ መሬት በማዘጋጀት፣ ከአካባቢው ለሚነሱ የልማት ተነሺዎች ምትክ መሬት በመስጠት ለፕሮጀክቱ ስኬት የከተማ አስተዳደሩ ድጋፍና ክትትልም ያደርጋል ነው ያሉት፡፡ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በተለያየ ጊዜያት ለከተማዋ ዕድገት ለሚያደርጉት አስተዋፅኦ አመስግነው በቀጣይ ከተማዋን የሚመጥን የንፁህ መጠጥ ውሃ ማስፋፊያ ፕሮጀክት እየተከናወነ ነው ያሉት ክቡር አቶ ከድር ጁሃር በበጀት ዓመቱ ተጠናቆ አገልግሎት ለመስጠት ጥረት ቢደረግም እየጨመረ ከመጣው ፍላጎት አንፃር በቀጣይ ሰፊ ስራ የሚጠይቅ በመሆኑ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የጥናት ሰነዶችን መነሻ በማድረግ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። በመድረኩ የድሬዳዋ ካቢኔ አባላት፣የሀገር ሽማግሌች፣ የከተማው ነዋሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡

Share this Post