ባለፋት አመታት ዘርፉ ባከናወናቸው ተግባራት ውጤታማ ስራ መስራቱ ተገለጸ።

ባለፋት አመታት ዘርፉ ባከናወናቸው ተግባራት ውጤታማ ስራ መስራቱ ተገለጸ።   ጥር 20/2018 ዓም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ሃብታሙ ኢተፋ ከሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ባለፋት ጊዜያት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል። ክቡር ሚኒስትሩ ሀገራችን ያላትን ሃብት በአግባቡ መጠቀምና መጠበቅ የሚያስችል በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ገልጸው በውሃ ሃብት አስተዳደር ዘርፍ የውሃ ሀብት እንዳይበከል የውሃ አካላት ዳርቻ ጥበቃ አዋጅ አጸድቀናል፣ በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር እንደሀገር ከ48ቢሊየን በላይ ችግኝ ተክለናል፣ በጎርፍ መከላከል ስራ የጎርፍ አደጋን መበቀነስ ወደ ልማት በማስገባት ዜጎችን ከመፈናቀል አድነናል ከዚህም በላይ በቀጣናው ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን እውን ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።   በተመሳሳይ በመጠጥ ውሃ ዘርፍ ከ80 ሚሊየን ህብረተሰብ የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ በማድረግ እና በሳኒቴሽን ስራ በ22 ከተሞች የፍሳሽ ማጣሪያ ፕሮጀክት ግንባታ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው; በኢነርጂ ዘርፍም ኢንዱስትሪዎች እንዲንቀሳቀሱ አድርገናል; ከዋና መስመር ርቀው ለሚገኙ ህብረተሰቦች በጸሀይ ሀይል እና ባዮ ጋዝ በመጠቀም የሀይል ተጠቃሚ ማድረግ በመቻሉ የደን መጨፍጨፍን በማስቀረት የካርበን ልቀትን መቀነስ ምርትና ምርታማነትን መጨመር መቻሉንም ገልጸዋል።   በዚህም የህዳሴ ግድብ ስንሰራ የነበረብንን ጫና አልፈን ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናው ብሎም በአፍሪካ ኩራት የሆነውን ግድባችን በማጠናቀቅ ከጎረቤት ሀገራት ጋርም በጋራ በዘላቂነት የማልማትና የማደግ ስራን እየሰራች ነውም ብለዋል።   የህዳሴ ግድብ ከሃይል ማመንጫነት ባሻገር የአካባቢው ህብረተሰቦች አሳን እያመረቱ እየተጠቀሙ ነው ከቱሪዝም ጋር ስራ ተጀምሯል በዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የንጋት ሀይቅ ማስተር ፕላን አዘጋጂቶ ይፋ አድርጓል ለአካባቢው የስራ እድል መፈጠሩንና ከዛም በላይ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ሌሎች ስራዎችን እንዲሰሩ እድል መፈጠሩን ገልጸዋል፡፡   እንደ ሀገር በገጠርና ከተማ ጽዱ ኢትዮጵያን ለመፍጠር በኮሪድር ልማት ፣ በወንዞች ዳርቻ አጠባበቅ እንዲሁም በመጸዳጃ ቤት ተጨባጭ ስራ መሰራታቸውን ገልጸው በቀጣይ ለሚካሄደው አፍሪካ ሕብረት አጀንዳ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።   የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤም ኢትዮጵያ በውሃ ደህንነትና ንጽህናቸው የተጠበቁ ከተሞችን ለመገንባት ያስመዘገበችውን ስኬት በተሞክሮነት ለማጋራት እንደሚሰራ በመጠቆም የዘንድሮው 39ኛ የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ’’ዘላቂ የውሃ አቅርቦትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የንጽህና አጠባበቅ ስርዓቶችን ማረጋገጥ፤ ለአጀንዳ 2063 ግቦች ስኬታማነት” በሚል መሪ ቃል ከየካቲት 7- 8/2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድም ገልጸዋል፡፡

Share this Post