የስርዓተ ጾታና ኢነርጂ ቴክኒካል የስራ ቡድን ውይይት አካሄደ።

የስርዓተ ጾታና ኢነርጂ ቴክኒካል የስራ ቡድን ውይይት አካሄደ።   ጥር 20/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የኢነርጂ ስራዎችን በተቀናጀ አግባብ ለማከናወን በሚያስችል መልኩ የተቋቋመው የስርዓተ ጾታና ኢነርጂ ቴክኒካል የስራ ቡድን ውይይት አደረገ። የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ የውብ ዳር አሚኖ የኢነርጂ ስራዎች በተቀናጀ መንገድ መሬት ላይ ወርደው የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በእውቀት፣ በገንዘብ እና በሀሳብ በመደጋገፍ ውጤታማ ስራ ለመስራት የሚቻልበት የስራ ቡድን ነው ብለዋል።   ቡድኑ 30 ዓባላት እንዳሉት የጠቀሱት ወ/ሮ የውብዳር አወቃቀሩ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተና በኢነርጂ ላይ ከሚሰሩ የመንግስት፣ የግል፣ መንግስታዊ ካልሆኑና ከሲቪል ማህበራት የተውጣጡ አባላትን ወደ አንድ በማምጣት ችግሮችን ለይተን እንዴት እንደምንሄድና በኢነርጂ ዙሪያ ያለውን አቅም ለማጠናከር የሚያስችል ነው ብለዋል። ቴክኒካል የስራ ቡድኑ ከተቋቋመ አንድ አመት ያስቆጠረ ሲሆን በዘርፉ ያለውን ክፍተት ለማወቅ በዩኤን ዲፒ በኩል የዳሰሳ ጥናት ተደርጎ ከኢነርጂ ጋር በተያያዘ እየተሰሩ ያሉና ሊሰሩ የታቀዱትን በመለየት በጋራ ለመስራት የሚያስችል እቅድ በማዘጋጀት ወደ ስራ የተገባ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።   የዛሬው ውይይት ዋና አላማም ባለፈው አንድ አመት ቆይታ ምንታቅዶ ምን ተከናወነ? ምን ቀረ ? ያልተተገበሩ ስራዎችን ከነ ምክንያታቸው እንዲሁም በቀጣይ ስራዎችን በምን መልኩ እናከናውን የሚለውን በመወያየት ውጤታማ ሰራ ለመስራት የሚያስችል ነው ብለዋል።   የአዴሌ ፕሮጀክት ጀንደር ስፔሻሊስት ወ/ሮ አምሳሉ ሁንዴ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ የታቀዱና የተከናወኑ እንዲሁም ያጋጠሙ ችግሮችን በዝርዝር አቅርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል። በውይይቱ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከኢትዮጽያ ሴቶች የኢነርጂ ባለሙያዎች ማህበር፣ ከኤስ ኤን ቪ፣ ከጅአይ ዜድ ኢትዮጽያ እና ሌሎችም የተወከሉ አባላት ተሳትፈዋል።

Share this Post