ከሞላው ማዕዳችን ሳይሆን ካለችን ጥቂት ነገር ተጋርተን በዓሉን በጋራ እናሳልፋለን። ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ

ከሞላው ማዕዳችን ሳይሆን ካለችን ጥቂት ነገር ተጋርተን በዓሉን በጋራ እናሳልፋለን። ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ   ታህሳስ 28/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ በተቋሙ ግቢ ውስጥ በተዘጋጀው የማዕድ ማጋራት መርሀግብር በቦሌ ክፍለከተማ፣ በቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 04 ለሚገኙ አቅመ ደካሞች እና ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ሰራተኞች የተለያዩ የበዓል መዋያ ግብዓቶችን ድጋፍ አድርጓል፡፡   መርሃ ግብሩን ያስጀመሩት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ከሞላው ማዕዳችን ሳይሆን ካለችን ጥቂት ነገር ተጋርተን በዓሉን በጋራ እናሳልፋለን ብለዋል፡፡ ክቡር ሚኒስትሩ አክለውም ያለውን ተካፍሎ አብሮ መብላት እና መጠጣት እንደ ኢትዮጵያውያን ትርጉም ያለው ተግባር በመሆኑ ባህላችንንና አንድነታችንን ለማስቀጠል በተለያየ ጊዜ በዓላትን ምክንያት በማድረግ ማዕድ ያጋርን ሲሆን በዛሬው ዕለትም ከባልደረቦቼ ጋር ከጎናችሁ መሆናችንን ለመግለፅ እወዳለሁ ብለዋል፡፡   በዓልን በዚህ መልኩ ለማክበር ሲታሰብ ለቤተሰቦቻችን አጋርነትን ለማሳያት፣ ከሞላው ማዕዳችን ሳይሆን ካለችን ጥቂት ነገር ተጋርተን፤ ሌሎችም እንደየአቅማቸው ተካፍሎ የመብላት ባህላችንን ጠብቀው እንዲያስቀጥሉ ለማድረግ፣ ለሌሎች መስጠትንና ካለን ላይ ማካፈልን ለማለማመድ ታሳቢ የተደረገ መሆኑንም ገልፀው፤ ለሁሉም መልካም በዓል እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡   በዕለቱ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለተቋሙ ሰራተኞች፣ ከቦሌ ክ/ከተማና ከወረዳ 04 ለተውጣጡ አቅመ ደካሞች በአጠቃላይ ለ435 ሰዎች ከ2.8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ለበዓል መዋያ የቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል። ድጋፍ የተደረገላቸው ሰዎችም መደሰታቸውን ገልፀው፤ የተቋሙን የበላይ አመራሮችንም ስለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።

Share this Post