ቴክኖሎጂን መጠቀም አማራጭ ሳይሆን ተመራጭ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
ታህሳስ 27/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በብቃትና ሰው ሀብት አስተዳደር ስራ አስፈፃሚ እና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስራ አስፈፃሚ በጋራ የተቀናጀ የሲቪል ሰርቪስ አስተዳደር መረጃ አያያዝ ስርዓትን /Integrated Civil Service Management Information System/ ለተቋሙ ሰራተኞች የአጠቃቀም ስልጠና ተሰጠ፡፡
በተቋሙ ወደ ሪፎርም ትግበራ ለመግባት የሚያስችል ስራዎች እየተሰራ በመሆኑ፤ ሪፎርሙ ተግባራዊ ሲሆን ቴክኖሎጂን መጠቀም አማራጭ ሳይሆን ተመራጭ ለማድረግ ከሚሰሩ ስራዎች መካከል አንዱና ዋነኛው የአቅም ግንባታ ስልጠና በመሆኑ የተቀናጀ የሲቪል ሰርቪስ አስተዳደር መረጃ አያያዝ ስርዓት /ICSMIS/ አጠቃቀምና አተገባበር ላይ ስልጠና ተሰጠ፡፡
ስልጠናውን ያስጀመሩት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የብቃትና ሰው ሀብት አስተዳደር ተወካይ ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ሔለን አበራ ስልጠናው በዘመናዊ የአሰራር ስርዓት ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲኖር በተቋሙ እየተሰራ ያለው የሪፎርም አካል በመሆኑ፤ በቀጣይ ወረቀት አልባ የአሰራር ስርዓትን ተግባራዊ በማድረግ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ያግዛል ብለዋል፡፡
ወ/ሮ ሔለን አያይዘውም የICSMIS መተግበሪያ ከብቃትና ሰው ሀብት አስተዳደር ስራ አስፈፃሚ የሚፈልጉትን አገልግሎት በሙሉ በአንድ ላይ አጣምሮ የያዘ በመሆኑ ሁሉም ሰራተኛ በግለታሪኩ ላይ የተጫነውን መረጃ በማየት ለማስተካከል ከወዲሁ የሚሰጠውን ስልጠና በአግባቡ እንዲከታተሉ አሳስበዋል፡፡
ስልጠናውን የሚሰጡት በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በ ICSMIS ፕሮጀክት የአይ.ቲ ሰፖርተር አቶ ጅክሳ ሰኚ የICSMIS ምንነትን፣ አስፈላጊነትንና ጠቀሜታን ለሰልጣኞች ግልፅ ካደረጉ በኋላ የተቀናጀ የሲቪል ሰርቪስ አስተዳደር መረጃ አያያዝ ስርዓት ዋናው አላማ የመረጃ ጥራትን ማሻሻል፣ ቀልጣፋ የአሰራር ስርዓት፣ ግልፀኝነት እና ውሳኔ አሰጣጥን ማሻሻል ነው ብለዋል፡፡
አቶ ጅክሳ በሲስተሙ አጠቃቀም ዙሪያ ከሰራተኞች ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተው፤ በቀጣይ ሲስተሙ ከቢሮ ውጪ መጠቀም የሚያስችል ስራዎችም እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ተቋሙ በቀጣይ ቴክኖሎጂን መጠቀም አማራጭ ሳይሆን ተመራጭ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ በመሆኑ ስልጠናው ሁሉንም ሰራተኞች ተደራሽ ለማድረግ በግማሽ ቀን ለሶስት ተከታታይ የስራ ቀናት የተሰጠ ሲሆን በቀጣይ ለስራ አስፈፃሚዎች የሚሰጥ ይሆናል።