የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የአገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የዝግጅት ምዕራፍ ስራዎች በሚጠበቀው ልክ እየተከናወኑ መሆኑን ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ገለጹ።
ቢሾፍቱ: ታህሳስ 26/2018ዓ.ም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብተሙ ኢተፋ በቢሾፍቱ ስራ አመራር ኢንስቲትዩት ተገኝተው የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የአገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም በዝግጅት ምእራፍ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን ተመልክተዋል።
እንደዘርፍ ተቀናጅተን በመናበብ ወደ ዝግጅት ምእራፍ ስራዎች መግባታችን ትልቅ አቅም በመፍጠር በጣም ጥሩ የሚባሉ ስራዎችን ለማከናወን አስችሎናል ብለዋል።
እንደ ተቋም የዲጅታል መተግበሪያዎችን በመጠቀም ስራዎች እየተተገበሩ መሆኑንና ተጠሪ ተቋማትም በዚሁ ልክ መተግበር እንዳለባቸው አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
ሪፎርም በባህሪው ልምምድን ይጠይቃል ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሊኖሩ የሚችሉ አንዳንድ የተዛቡ አመለካከቶችን ለመቅረፍ በሚቀጥሉት ሳምንታት ከሰራተኛው ጋር በሚገባ ውይይት እና የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ይሰራልም ብለዋል።
ከሰነድ ዝግጅት ጎን ለጎንም ተቋምን ምቹና ማራኪ ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ በመሆኑ ሴቶችን እና አካል ጉዳተኞችን የሚመለከቱ ጉዳዮች እየተተገበሩ የሚመሩበት አሰራር ተዘርግቷልም ብለዋል።
በሚኒስትር ዴኤታ ማእረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪና ውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የአገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የአብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ በየሳምንቱ ኮሚቴው በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንዳለ ገልጸው የሚቀሩ ሰራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል ብለዋል።
እያንዳንዱ ዶክመት በሚገባ ተሰንዶ ሊቀመጥ እንደሚገባና በእቅዳችን መሠረት የትግበራ ስራዎችን ከወዲሁ ትኩረት እያደረግን መሰራት ይጠበቃልም ብለዋል።
ስራው ለፍሬ እንዲበቃ በተጀመረው መነቃቃት መተግበር ግድ ይላል ፤ ለዚህ ደግሞ አብይ ኮሚቴው የሚያደርገውን ድጋፍና ክትትል አጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተርና በአለም የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት የአፍሪካ አህጉር ፕሬዝዳንት እና የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የአገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የአብይ ኮሚቴ አባል አቶ ፈጠነ ተሾመ በየአምዱ የተዘጋጁ ሰነዶች የኮሚቴውን የመፈጸም አቅም እጨመረ መምጣቱን አመላካች እንደሆኑና በከፊል ወደ ትግበራ እንድንገባ የሚያስችሉም ናቸው ብለዋል።
በየአምዱ ያሉ ቡድኖች በቀጣም በመተጋገዝ ከተገበሩ ትልቅ ውጤት እናስመዘግባለን ብለዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ኃላፊና የውሃና ኢነርጂ ዘርፍ የአገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም የአብይ ኮሚቴ አባል ዶ/ር አረጋዊ በርሔ ከኮሚቴ አወቃቀሩ ጀምሮ ውጤታማ ስራ እየተሰራ መሆኑ የተዘጋጁ ሰነዶች ማሳያ ናቸው ብለዋል።
የተጀመረውን የተነሳሽነት መንፈስም እስከ ትግበራ ማስቀጠል ከዚህ ኮሚቴ የሚጠበቅ ነውም ብለዋል።