በባዘርኔት ፕሮጀክት የሚተገበረው የአዋሽ ተፋሰስ የነባራዊ ሁኔታ የግምገማ ሪፖርት ማረጋገጫ አውደ ጥናት ውይይት እየተካሄደ ነው።

በባዘርኔት ፕሮጀክት የሚተገበረው የአዋሽ ተፋሰስ የነባራዊ ሁኔታ የግምገማ ሪፖርት ማረጋገጫ አውደ ጥናት ውይይት እየተካሄደ ነው። አፋር ሰመራ ታህሳስ 9/2018ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በባዘርኔት ፕሮጀክት የሚተገበረው የአዋሽ ተፋሰስ ነባራዊ ሁኔታ የግምገማ ሪፖርት ማረጋገጫ አውደ ጥናት የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክ በያንጉዲ ሆቴል እየተካሄደ ነው።   በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለፁት ኢትዮጵያ ያሏት12 ተፋሰሶች ቢሆኑም በተፋሰስ አስተዳደር በሚተገበሩ ስራዎች በስፋት ማዳረስ አስፈላጊ በመሆኑ ለዚህ ተግባር የዘርፉ አመራር ሚና የጎላ ሊሆን ይገባል ብለዋል። በተጨማሪም በተፋሰስ አስተዳደር ለሚተገበሩ የውሃ ሀብት አስተዳደር ስራዎች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሰጠው ትኩረት መሰረት በቂ የሰው ሃይልና በጀት በመኖሩ ለፕሮጀክቱ ማጠናቀቂያ በታቀደው የጊዜ ገደብ ውስጥ ሰፊ ስራ መስራትና አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ይጠበቅብናል ብለዋል።   በተጨማሪም የአዋሽ ባዘርኔት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ዮሃንስ ዘሪሁን እንደገለፁት ባዘርኔት ፕሮጀክት አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደሮችን ከአየር ንብረት ለውጥ፣ከድርቅ፣ከጎርፍና ከሌሎች ተፈጥሯዊ ጉዳቶች ለመጠበቅ በመካከለኛውና በታችኛው አዋሽ ተፋሰስ ውስጥ የተፋሰስ እንክብካቤ በማድረግ ውሃና ግጦሽ ፍለጋ የሚሰደዱትንና ተጎጂ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ የጎላ አስተዋፅኦ ያበረክታል ብለዋል። እንዲሁም የአፈር መከላትና የተፈጥሮ መጎሳቆልን ለመቀልበስ የሚሰሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።   እንዲሁም በጣሊያን ትብብር በ31.5 ሚሊዮን ዩሮ የሚደገፈው የባዘርኔት ፕሮጀክት በአዋሽ ተፋሰስ በሚከናወኑ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ስራዎች የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና ለአካባቢው ማህበረሰብ ህልውና ትልቅ እድል ናቸው ያሉት በመድረኩ ላይ የተገኙት የጣሊያን የልማት ትብብር ኤጀንሲ ( Italian agency for development cooperation ) የዋሽ፣ ኢንቫሮመንት እና ኢነርጂ ሴክተር ማናጀር ሚስተር ፋቢዎ ጋጊ (Fabio Gaggi) ናቸው።   በመድረኩ ላይ የተሳተፉት የሚኒሰቴር መስሪያ ቤቱ አማካሪዎች፣ የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደር ስራ አስፈፃሚዎች፣የፕሮጀክት አስተባባሪዎች ፣ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና የክልል የፕሮጀክቱ አስፈፃሚዎች በቀረቡ የነባራዊ ሁኔታ ግምገማ ሪፖርቶች ላይ በስፋት ውይይት እያካሄዱ የሚገኙ ሲሆን የመርሃግብሩ አካል የሆነው የመስክ ጉብኝት በቀጣይ ቀን እንደሚካሄድ ተገልጿል ።

Share this Post