ወንድማማችነታችንን ለማጠናከር በውሃና ኢነርጂው ዘርፍ በጋራ እንሰራለን።
=======================
ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ
ታህሳስ 08/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ለደቡብ ሱዳን የውሃ ሀብት እና መስኖ ሚኒስቴር ለመጡ ልዑካን የተዘጋጀው የልምድ ልውውጥ እና የአቅም ግንባታ ስልጠና ማጠቃለያ መርሀ ግብር ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ባደረጉት ንግግር ወንድማማችነታችንን ለማጠናከር በውሃና ኢነርጂው ዘርፍ በጋራ እንሰራለን ብለዋል።
ባለፈው ወር የተከበረው የውሃና ኢነርጂ ሳምንት ላይ በጋራ ለመስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይም መወያየታቸውን ያስታወሱት ክቡር ሚኒስትሩ ከደቡብ ሱዳን ጋር የጋራ ማንነት፣ አንድ ህዝብና አንድ ወንዝ የምንጋራ በመሆኑ በስልጠናም ሆነ በልምድ ልውውጥ የተገኘውን ተሞክሮ እንዴት በተሳካ ሁኔታ ማከናወን እንችላለን የሚለውን ማየት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትሩ አክለውም ለልዑካን ቡድኑ ልምድ ያጋሩ ተቋማትን እና ስልጠናው ያመቻቹትንም አመስግነዋል፡፡
በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄኔራል ዘሪሁን አበበ በበኩላቸው የደቡብ ሱዳንና ኢትዮጵያ የቆየ ወንድማማችነት ግንኙነትን ማስቀጠል እንደሚገባ ገልፀው፤ የስልጠናውን ዓላማ ተረድተው ወደ ተግባር መቀየር እንዳለባቸው ብሎም የወንድማማች ግንኙነታችንን ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ለአንድ ሳምንት ሲሰጥ የነበረው በመስክ ምልከታ የተደገፈው የአቅም ግንባታ ስልጠና እና የልምድ ልውውጥ ውጤታማ መሆኑን የገለፁት በኢትዮጵያ የደቡብ ሱዳን አምባደር Boutros Thok Deng ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር እንደ አንድ ስታፍ በጋራ እንሰራለን፤ በውሃና በኢነርጂውም ዘርፍ እየተሰራ ያለው ስራ እንደምርጥ ተሞክሮ የምንወስደው ሲሆን በጉብኝቱ ጊዜ ለተባበሩን ተቋማትም እናመሰግናለን ብለዋል፡፡
በስልጠናው ለተሳተፉ የሚኒስቴር መ/ቤቱ እና የደቡብ ሱዳን ልዑካን የምስክር ወረቀት የተበረከተላቸው ሲሆን በመርሀግብሩ የሚመለከታቸው የተቋሙ አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።