ለፕሮጀክቶች ውጤታማነት የአመራር ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው ተባለ።

ለፕሮጀክቶች ውጤታማነት የአመራር ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው ተባለ። ጎዴ/ቀላፎ፦ ታህሳስ 04/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በውሃ ሀብት አስተዳደር ከሚተገበሩ ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነው የባዘርኔት ፕሮጀክት በሶማሌ ክልል የቀላፎ ወረዳ አሎ አጋርሲ ተፋሰስ በተጎበኘበት ወቅት ለፕሮጀክቶች ውጤታማነት የአመራር ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑ ተገለፀ።   የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር በባህሪው የቅንጅት ስራ የሚፈልግ ነው፤ ያሉት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የባዘርኔት ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሞላ ረዳ የተጀመረው ስራ ከክልሉ ግብርና እና ከአካባቢ ጥበቃ ቢሮዎች ጋር በጋራ የተፋሰስ አስተዳደርና መልሶ ማገገም (Rehabilitation) ስራዎች ማህበረሰቡን በማሳተፍ የጎርፍ ስጋት ጥያቄን የሚመልስ ስራ ይሰራልም ብለዋል።   የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ፅ/ቤት ም/ኃላፊ አቶ መሀመድ ዩሱፍ ፕሮጀክቱ የህዝቡን ጥያቄ በሚመልስ መልኩ መጀመሩን ለማረጋገጥ የተደረገው የመስክ ምልከታ ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት የሚያመላክት በመሆኑ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩልም ቀሪ ስራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ውጤታማ ስራ በጋራ እንሰራለን ብለዋል።   የሶማሌ ክልል የውሃ ቢሮ ኃላፊ ኢ/ር አህመድ ሚራድ በበኩላቸው የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በጣሊያን መንግስት በተገኘ ድጋፍ ከሶማሌ ክልል የውሃ ቢሮ እና አጋር አካላት ጋር በመተባበር ለ3 አመታት የሚተገበረው ፕሮጀክት በዋቢሸበሌ ተፋሰስ አካባቢ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍልን ኑሮ ለማሻሻል ስለሚያስችል እስከታችኛው መዋቅር ድረስ የድርሻውን እንደሚወጣ፤ በክልሉ በኩልም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም አሳስበዋል።   የጉብኝቱ ዓላማ ፕሮጀክቱ የሚተገበርበት ሳይት ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው የሚለው ለማረጋገጥ እና የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን ተግባራዊ ለማድረግ ምን ምቹ ሁኔታዎች አሉ፤ የአካባቢው ማህበረሰብስ በምን አግባብ ቢመራው ነው ውጤታማ የሚሆነው የሚለውን ለመገምገም ቀላፎ ወረዳ አሎ ኢጋርሲ ቀበሌ ነዋሪዎች ጋር ስለሚከሰተው የጎርፍ ክስተት እና ጎርፍን እንዴት ወደ ሀብት መቀየርና በዘላቂነት መከላከል በሚቻልበት ሁኔታ ብሎም በሚተገበረው ፕሮጀክት ዙሪያ የሚመለከታቸው የክልሉ ቢሮ ኃላፊዎች ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ውይይት አካሂደዋል።   የአካባቢው ነዋሪዎችም ለፕሮጀክቱ ተግባራዊነት አስተዋጽኦ እናበረክታለን፤ የዚህ ፕሮጀክት ተጠቃሚ እንድንሆን ያደረጉንን የመንግስት መስሪያ ቤቱንም ሆነ ክልሉን እናመሰግናለን ብለዋል።

Share this Post