የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት ከስምንት አማካሪዎች ጋር የውል ስምምነት ተፈራረመ

የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት ከስምንት አማካሪዎች ጋር የውል ስምምነት ተፈራረመ ህዳር 24/2018 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ የከርሰ ምድር ውሃ ፕሮጀክት ከስምንት አማካሪዎች ጋር የውል ስምምነት ተፈራረመ፡፡   የውል ስምምነቱን የፈረሙት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር አስፋው ዲንጋሞ ናቸው፡፡ የማህበረሰቡን የመጠጥ ውሃ ተደራሽነት ለማስፋት በሚደረገው ጥረት እንደአጠቃላይ በፕሮጀክቱ ከተያዙት 110 ፕሮግራሞች ውስጥ በ55 ወረዳዎች በሚተገበሩ የንጹህ መጠጥ ውሃ ግንባታ ስራዎች የአቅም ግንባታና ከግንባታ በኋላ የፕሮጀክቶችን ቀጣይነት ለማረጋገጥ እንዲያስችል ከአማካሪዎቹ ጋር ውል መግባት ማስፈለጉን ክቡር አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡   አብዛኞቹ አማካሪዎች ቀደም ሲል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሚያካሂዳቸው ተመሳሳይ ስራዎች የማማከር አገልግሎት ሲሰጡ እንደነበር ክቡር አምሳደሩ አስታውሰው በዘርፉ ሰፊ ልምድ ያላቸው በመሆኑ በቀጣይ በሚኖራቸው የጊዜ ቆይታም ይህንን ተግባር አጠናክረው በማስቀጠል ፕሮጀክቶችን ለፍጻሜ ማድረስ እንዳለባቸው ክቡር አምሳደሩ በአጽንዖት ተናግረዋል፡፡   አማካሪዎቹ በበኩላቸው በማማከር አገልግሎቱ በተሰጣቸው የስራ እድል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን በማመስገን ፕሮግራሞቹ በታቀደላቸው ጊዜ እንዲከናወኑ በታማኝነትና በትጋት ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡   የስምንቱ አማካሪዎች አጠቃላይ የውል ዋጋ 213,385,950.00 ብር እና 1,634,279.78 ዶላር ሲሆን ወጪው የሚሸፈነው ሙሉ በሙሉ ከአለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ መሆኑም ተገልጿል፡፡ የማማከር አገልግሎቱ የተቀመጠለት የውል ጊዜ በሚቀጥሉት 18 ወራት የሚጠናቀቅ ይሆናል ተብሏል፡፡

Share this Post