በኃይል አቅርቦት ኢንቨስትመንት ላይ ለመሠማራት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩ ተገለጸ።
ነሐሴ 8/2017(ውኢሚ)፦በኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ በኃይል አቅርቦት ኢንቨስትመንት ላይ የሚሰማራበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ገለጹ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከዓለም አቀፍ ሶላር አሊያንስ ጋር በፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂ የሶላር ሚኒግሪድና የሶላር ፓርክ ፕሮጀክት ለመገንባት ስምምነት መፈራረማቸው በሶላር ፓርክና የሶላር ሚኒ ግሪድ የኃይል ማመንጫ፣ በመስኖና መጠጥ ውሃ አቅርቦት የፋይናንስና የቴክኖሎጂ ትብብር ዕድሎችን የሚያመቻች መሆኑን ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡
የፀሐይ ኃይል ልማት ተደራሽነት የዜጎችን ሕይወት ለማሻሻል ትልቅ ሚና እንዳለው እና የግሉ ዘርፍ የልማት ተዋናዮችም በኢትዮጵያ የፀሐይ ኃይልና የግብርና ልማት ኢንቨስትመንትን ማሳደግ የሚያስችል ፖሊሲ ስራ ላይ በመዋሉ ለግሉ ዘርፍ ኢንቨስት መንት በር ጥሩ እድል የሚፈጥር ነውም ብለዋል፡፡
የዓለም አቀፍ ሶላር አሊያንስ ዋና ዳይሬክተር ሚስተር አሺሽ ከሀን የዓለም አቀፍ የፀሀይ ኃይል ጥምረት ኢትዮጵያን ጨምሮ 124 አባል ሀገራትን በማቀፍ የፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂ ልማትን ለማስፋፋት እና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየሰራን ነው ብለዋል።
በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የግብርና ምርታማነትን የሚያሳድጉ በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ አነስተኛ የኤሌክትሪክ አቅርቦቶችን በማስፋት የውሃ ፓንፖችን ለማልማት ድጋፍ እንደሚደርጉም ነው ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡
የኢትዮጵያ የፀሐይ ኃይል ልማት ማህበር ዋና ዳይሬክተር የምስራች ሲሳይ በዘርፉ ላይ በፖሊሲ ማማከር፣ የፋይናንስ ማፈላለግና የአቅም ግንባታ ተግባራትን እያከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በዓለም አቀፍ ሶላር አሊያንስ ጥምረት አዘጋጅነት በፀሐይ ኃይል ልማት የፋይናንስ ዕድሎች ዙሪያ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ሙያተኞች በተገኙበት የምክክር መድረክ ተካሂዷል።