የቅድመ አፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ የውሃና ኢነርጂ ኤግዚቢሽን ላይ ለዕይታ የቀረቡ የፈጠራ ስራዎች ንጹህ ኢነርጂን ተደራሽ በማድረግ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ድርሻቸው የላቀ ነው ተብሏል፡፡
ነሃሴ/8/2017ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የቅድመ አፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ የውሃና ኢነርጂ ኤግዚቢሽን ላይ ለዕይታ የቀረቡ የፈጠራ ስራዎች ንጹህ ኢርጂን ተደራሽ በማድረግ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ድርሻቸው የላቀ ነው ተብሏል፡፡
ያነጋገርናቸው የኢንተር ኢትዮጵያ ፒ ኤል ሲ ስራ አስኪያጅ አቶ አሮን ነብዩ ድርጅታቸው ያገለገሉ የሶላርና የተለያዩ የኤሌክሮኒክ እቃዎችን በመሰብሰብ ታድሰው መልሰው አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ በተመጣጣኝ ዋጋ በተለይም ለገጠሩ ማህበረሰብ ተደራሽ እንዲሆኑ ከፍተኛ ስራ እየሰሩ መሆኑን ነግረውናል፡፡
ድርጅቱ ስራውን ለመስራት ውጭ ሀገር ካሉ ማኑፋክቸሮች ጋር ውል ወስዶ አግልግሎት የማይሰጡ የኤሌክትሮኒክ እቃዎችን በመሰብሰብና በማደስ በትንሽ ትርፍ 75 በመቶ ቅናሽ ተደርጎበት መልሶ ለተጠቃሚው የማድረስ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በፈረንጆቹ 2025 ሰርቪያ ላይ በነበረው የሳስቴኔቢሊቲ ውድድርም ከተሳተፉ 100 ሀገራት በፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ አንደኛ በመውጣት የሰርተፍኬት ሽልማት አግኝተናል ብለዋል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥም አካባቢን ሊበክሉ የሚችሉ 3 ሺ ሶላር ሆም ሲስተሞች ታድሰው ለአገልግሎት መብቃታቸውን የገለጹት ስራ አስኪጁ 45 ሺ ኪሎግራም የሚመዝኑ ከአገልግሎት ውጭ የሆኑ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን በመሰብሰብ አካባቢን ከብክለት መታደግ ተችሏል ብለዋል፡፡ ለተሻለ ነገር እንስራ ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ሌላኛው ያነጋገርናቸው አቶ ዮሃንስ አየለ የአማሔ ማኑፋክቸሪግ ኃ/የተ/የግል ማህበር ስራ አስኪያጅ ድርጅቱ 14 ዓይነት የእንጀራ ምጣዶችን 8 ዓይነት ምድጃዎችን በተለያዩ ዲዛይኖች ለአጠቃቀም ምቹና ማራኪ በሆኑ ማቴሪያሎች ተዘጋጅተው በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚዎች እያቀረቡ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
ምርቶቹ ለአጠቃቀም ምቹ ከመሆናቸው ባሻገር ሀይል ቆጣቢ መሆናቸው ከኢትዮጵያ ነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን የሀይል ቆጣቢ እና የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ማግኘታቸው፣ ምርቶቻቸው ለምግብ ማብሰል ተስማሚ በሆኑ አሉሙኒየም የተሰሩ መሆናቸው ፣ የተሟላ ዋስትና ያላቸው ፣ የመብራት ፍጆታን የሚቀንሱ ፣ሀገራዊ የኤሌክትሪክ ብክነትንና የአየር ብክለትን የሚቀንሱ ፣ የደን መመናመንን የሚከላከሉ ፣የውጭ ምንዛሬን የሚቀንሱ እና ለአረንጓዴው አለም አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ መሆናቸው ተመራጭ እንደሚያደርጋቸውም ነው የገለጹልን፡፡
ከዚህም ባሻገር በቀላሉ የሚጠገኑና መለዋወጫ ያላቸው ሲሆን ድርጅቱ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየሰራ እንደሚገኝና በኢነርጂ ዘርፍ ላበረከተው አስተዋጽኦም የዋንጫ ተሸላሚ መሆኑን ማወቅ ተችሏል፡፡
ማህበረሰቡ ምጣዶችንም ሆነ ስቶቮችን ሲገዛ የሀይል ቆጣቢነታቸውን ማረጋገጫ እያየ ቢገዛ ለራሱ ከመጠቀም ባለፈ የኢነርጂ ፍጆታን በመቀነስ ረገድ የሚደረገውን ጥረት አጋዥ ይሆናል ሲሉም ነው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት፡፡