ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጋጭነትን ከመቀነስ አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተች መሆኑን ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ገለጹ፡፡
ነሃሴ 6/2017ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ የቅድመ ሁለተኛ የአፍሪካ አየር ንብረት ሰሚት የውሃና ኢነርጂ አውደ ርዕይን በይፋ በከፈቱበት መድረክ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጋጭነትን ከመቀነስ አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ በኢትዮጵያ የሙቀት መጠንን በመጨመር ፣የዝናብ ወቅትን በማዛባት ፣ የዝናብ መጠንን በመቀነስ ፣ለጎርፍና ድርቅ ተጋላጭነትን በመጨመር የሚያመጣው ተጽእኖ ክፍተኛ ነው ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ይህን ተጽእኖ ለመቋቋም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጅ በመቅረጽ ፣ ብሔራዊ የመላመድ እቅድ በማዘጋጀት እንዲሁም የረጅም ጊዜ የካርበን ልቀት ቅነሳ ስትራቴጅ በመቅረጽ እየተተገበረ ይገኛል ብለዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ ባለፉት 7ዓመታት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ለሌሎች ሀገራትም ተሞክሮ የሆኑ 47.7 ቢሊየን ችግኞች መተከላቸው ትልቅ ማሳያ መሆኑንና በቀጣይም በዘርፉ ጠንካራ ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነትን ከመቀነስ አኳያ የምታበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ቢሆንም የበካይ ጋዝ ቅነሳ ድርሻዋ ከአለም 0.04 ከመቶ ብቻ ነው ያሉት ክቡር ሚኒስት ዴኤታው ይህ መስዋትነት የሚከፈለው ለአለም አቀፉ ህጎች ተገዥ በመሆኗ ብሎም አብዛኛው ኢኮኖሚያችን በግብርናው ላይ ጥገኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ይህ ዘርፍ እንደይጎዳ አስቀድመን መስራት ስለሚገባን ነው ብለዋል፡፡
የቅድመ ሁለተኛ የአፍሪካ ክላይሜት ሰሚት የውሃና ኢነርጂ አውደርዕይ ዋና ዓላማም አፍሪካ በአፍሪካ የሚመራ የአየር ንረት ለውጥ መፍትሔዎች እንዳሏት ለአለም ህብረተሰብ ለማሳወቅ፣ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ፣በአረንጓዴ ልማት የምትሰራው ስራ ምን ያህል የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እያደረገችው ያለውን ጠንካራ ስራ ለማስተዋወቅ ፣ የአየር ንረት ለውጥን መቋቋም የሚችል አቅም ለመገንባት እና የአፍሪካውያንን የጋራ አቋም በመገንባት በጋራ ለመስራት እድል የሚፈጥር ሲሉ ገልጸውታል፡፡
በአውደ ርዕዩ የመንግስት ተቋማት ፣ የክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ፣ የልማት አጋሮች ፣ የዘርፉ ተመራማሪዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው አካላት እየተሰተፉ ሲሆን ከ30 በላይ የሶላር አቅራቢና ከ20 በላይ የሚሆኑ የልማት ድርጅቶች ስራዎቻቸውን እያስጎበኙ ነው፡፡