ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በደቡብ ምእራብ ሸዋ ዞን ኢሉ ወረዳ በጣለዉ ከባድ ዝናብ የተነሳ ሁለት ቀበሌዎች ላይ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አደረገ።

ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በደቡብ ምእራብ ሸዋ ዞን ኢሉ ወረዳ በጣለዉ ከባድ ዝናብ የተነሳ ሁለት ቀበሌዎች ላይ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አደረገ። ሀምሌ 30/2017ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ የተመራ ቡድን በኢሉ ወረዳ ተጅና አስጎሪ ቀበሌዎች የደረሠውን የጎርፍ አደጋ በስፍራው ተገኝተው ተመልክተዋል። ቡድኑ ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ4ሚሊየን ብር በላይ በሚሆን ወጪ የንጽህና መጠበቂያ ሳሙናዎችን እና የውሃ ማከሚያ ኬሚካሎች በስፍራው ተገኝቶ ድጋፍ አድርጓል። ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ ለችግሩ አስቸኳይ መፍትሄ ለማበጀት ከወረዳው አስተዳደር ፣ ከኮንትራክተሮች ፣አማካሪዎች ፣ ከሀይማኖት አባቶችና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር መክረዋል። ለችግሩ ዘላቂነት ያለው መፍትሄ ለመስጠት ጥናቶች እየተጠኑ መሆኑንና ከውጤቱ በመነሳት የሚሰራው ስራ እንዳለ ሆኖ አሁን ላይ ግን አስቸኳይ መፍትሄ መስጠት እንደሚገባና እንደሚኒስቴር መስሪያ ቤትም ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። የጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ተመስገን ከተማ ክልሉ ፣ ዞኑ ፣ ወረዳውና አጠቃላይ ማህበረሰቡ በንቃት መከታተል እንደሚገባውና ስራው ለውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ብቻ የሚተው አለመሆኑን ገልጸው ማሽን መግባት በሚቻልባቸዉ ቦታዎች ከወረዳው ጋር በመሆን ጥገና እንዲደረግና ማሽን በማይገባባቸው አካባቢዎች ደግሞ ከአደጋ ስጋት ኮሚሽን በተገኘው የማዳበሪያ ድጋፍ አፈር በመሙላት አስጊ በሆኑ ቦታዎች ስራዎች እንደሚሰሩ ገልጸዋል። የኢሉ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ታደለ ተስፋ አካባቢው በተፈጥሮ ለጎርፍ አደጋ ስጋት ተጋላጭ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባለፈውና በዘንድሮ ዓመት ቀድሞ የጎርፍ መከላከል ስራ ባይሰራ ኖሮ ችግሩ ከዚህም የከፋ ይሆን ነበር ለዚህም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሊመሠገን ይገባል ብለዋል። በወረዳው አራት ቦታዎች ሰብሮ የወጣው ጎርፍ ተጂና አስጎሪ ቀበሌዎች ላይ ጉዳት አድርሷል ብለዋል። በጉዳቱ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ከፌደራል ጀምሮ እሰከ ወረዳ የምግብ ፣ የአልባሳት የንጽህና መጠበቂያ እና የህክምና ድጋፍ እየተደረገላቸው ሲሆን ለከብቶቻቸውም መኖ እየቀረበ ነው ብለዋል። እየተደረገ ያለው ድጋፍ እንዳለ ሆኖ በዘላቂነት ለማቋቋም ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያስፈልግም ነው አስተዳዳሪው የጠየቁት።

Share this Post