በዝዋይ ሻላ ንኡስ ተፋሰስ የሚተገበረው የሙከራ ፕሮጀክት ሰፋ ወዳለ ተፋሰስ ከፍ ተደርጎ ሊሰራበት በሚችል መልኩ ውጤታማ መሆኑ ተገለጸ።
ነሃሴ 29/2017ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) በአፍሪካ ልማት ባንክ የ 1 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ በዝዋይ ሻላ ንኡስ ተፋሰስ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚያስችል ማህበረሰብ የመፍጠር ፕሮጀክት ሰፋ ወዳለ ተፋሰስ ከፍ ተደርጎ ሊሰራበት በሚችል መልኩ ውጤታማ መሆኑ ተገልጿል።
ፕሮጀክቱን አስመልክቶ በተዘጋጀው አውደ ጥናት ያነጋገርናቸው ፕሮፌሰር መኩሪያ አርጋው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢ ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ውሃን መሠረት ያደረገ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ማህበረሰብና ስነምህዳር ለመፍጠር በሚያስችል መልኩ ተቀርጾ ተግባራዊ የሆነው ፓይለት ፕሮጀክቱ ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ የሚተገበርበት አካባቢ በርካታ የልማት እንቅስቃሴዎች የሚካሄዱበት እና የውሃና የመሬት ሽሚያ ያለበት በመሆኑ ከዝናብ ማጠርና ከሙቀት መጨመር ጋር ተያይዞ በምርት ፣ በውሃ ሀብት ፣ በሰውና በአካባቢ ስነምህዳር ላይ የሚያመጣው ተጽእኖ ከፍተኛ ነው ያሉት ፕሮፌሰሩ የአየር ንብረት ለውጥን መቀልበስ ባይቻልም ተቋቁሞና ተላምዶ የመኖር ስርዓትን ለመገንባት እንዲቻል ፕሮጀክቱ ጥሩ ማሳያ ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ሲቀረጽ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመቋቋም በውሃው ሴክተር ሴቶችን ማእከል አድርገው የተሰሩ ስራዎችን በመፈተሽ ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ የማይበገር ስነምህዳርና ማህበረሰብ መገንባት እንዲቻል በእቅድ ውስጥ የተካተቱ ስራዎችን በመገምገም እና መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ እውነታ በባለሙያዎች በማጥናት ክፍተትን ሊሞላ የሚችል የአቅም ግንባታ ስልጠና ላይ ትኩረት በማድረግ በተመረጠው ንኡስ ተፋሰስ ማህበረሰቡንና ስነምህዳሩን ሊቀይሩ የሚችሉ ስራዎችን ሰርተን ማሳየት ችለናል ብለዋል ፕሮፌሰሩ።
በአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ሴቶች የበለጠ ተጎጅ ናቸው ያሉት ፕሮፌሰሩ ይህንን ለመቋቋም በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስራዎች እንዲሳተፉ ፣ የአካባቢያቸውን የውሃ ሀብት የማልማት፣ የመምራትና ውሳኔ የመስጠት ተግባራት ላይ እንዲሳተፉ ለማድረግ ከፌደራል ጀምሮ እሰከ ወረዳ ሁሉም የድርሻውን ወስዶ በቅንጅት በአጭር ጊዜ ውጤታማ ስራ የሠራንበት ማሳያ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በሚተገበርበት ወረዳ ያሉ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ወጣቶችንና ሴቶችን በማደራጀት፣ ህጋዊ እውቅና እንዲኖራቸው በማድረግ ፣የመተዳደሪያ ደንቦችን በማዘጋጀት እና በማጽደቅ ፣የንቅናቄ ስራዎችን በሚገባ በመተግበር በኩል ከፍተኛ ስራዎችን መሰራታቸውንም ፕሮፌሰሩ አክለው ገልጸዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የውሃ ሀብት አስተዳደር መሪ ስራ አስፈጻሚው አቶ ደበበ ደፈርሶ ፕሮጀክቱን ልዩ የሚያደርገው የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉና የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን በምግብ ራስን ከመቻል ጋር በማስተሳሰር የሚተገበር መሆኑ ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ወደ ማጠናቀቂያው በመድረሱ የተገኙ ውጤቶች ተፈትሸው አንድ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደርን የምናሳይበት ነውም ብለዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቀጣይ እንደነዚህ አይነት ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ስለሚያደርግ ሌሎች ተቋማትም ሆኑ አጋር አካላት በዚህ አይነት አግባብ መጥተው ስራቸውን በጋራ እንዲያከናውኑ እናበረታታለን ብለዋል አቶ ደበበ።
ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት ጊዜአቸውንና እውቀታቸውን ላበረከቱ ዩኒቨርሲቲዎች ፣ከፌደራል ጀምሮ እስከ ወረዳ ላሉ ሴክተር መስሪያ ቤቶች በተለይም የዝዋይ ሻላ ንኡስ ተፋሰስ አጋሮች ላበረከቱት ትልቅ አስተዋጽኦ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስም አመስግነዋል።
ፕሮጀክቱ በሚታዩ ጉዳዮች ላይ በተጨባጭ አቅም የገነባ በመሆኑ ቀጣይ ሆኖ የሚተገበር ይሆናልም ብለዋል መሪ ስራ አስፈጻሚው።