የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ተፋሰስን ተደራራቢ ችግሮች ለመፍታት በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ ገለጹ።
ሀምሌ 29/2017ዓ.ም (ው.ኢ ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ በተዘጋጀው አውደ ጥናት መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ክቡር አቶ ሞቱማ መቃሳ የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ተፋሰስን ተደራራቢ ችግሮች ለመፍታት በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ የመጣውን የሀገራችን የውሃ ሀብት ችግሮች ለመፍታት በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ነው ያሉት አማካሪው በተለይም ስር የሰደደ ችግር ያሉበትን የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ተፋሰስን ተደራራቢ ችግሮች ለመፍታት መንግስት ከሚያደርጋቸው ጥረቶች ጎን ለጎን መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ አጋር አካላት ጋር እንዲሁም አለም አቀፍ የልማት ድርጅቶችን በማስተባበር ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
የአውደ ጥናቱ ዋና አላማም በመካከለኛው ስምጥ ሸለቆ ተፋሰስ አካባቢ ውሃን መሠረት ያደረገ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖን ለመቋቋም የሚያስችል የመስክ ትግበራና የአቅም ግንባታ ስራዎችን በማከናወን አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር ነው ብለዋል ክቡር አቶ ሞቱማ።
ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ማእከል ጋር በጋራ የአየር ንብረት ለውጥን በተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ስልት ችግሩን የሚቋቋም ማህበረሰብ ለመፍጠር ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ ድጋፍ ባለፉት 13 ወራት ሰፋፊ ስራዎች እየተሠሩ መሆኑን ነው አማካሪው የገለጹት።
ከችግሩ ስፋት አኳያ ሁሉንም አካባቢዎች በአንድ ጊዜ ተደራሽ ማድረግ አይቻልም ያሉት አማካሪው የተገኘውን ውስን ሀብት ችግሩ በሰፋበትና በተመረጠ ሰርቶ ማሳያ አካባቢ ጥሩ ተሞክሮ ሊሆን በሚችል መልኩ በመተግበር ወደ ሌሎች ክልሎችና ወረዳዎች ማስፋፋት በሚያስችል መልኩ እየተተገበረ ነው ብለዋል።
በፕሮጀክቱ ትግበራ በሰዎች ህይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንና የተፈጥሮን መራቆት ማከሚያ ዘዴዎችን በተቀናጀ የውሃ ሀብት ማኔጅመንት ስልት፣የአየር ንብረት ለውጥ ችግሮችን የሚቋቋም፣ ችግሩ ከተከሰተም በፍጥነት የሚያገግም ዘላቂነት ያለው የኢኮኖሚ አቅም ለመፍጠር ማህበረሰቡን እያገዘ ይገኛልም ብለዋል።
የተጀመሩ ስራዎች ከፕሮጀክቱ በኋላ ቀጣይነት እንዲኖራቸው ከፌደራል ጀምሮ በየደረጃው ላሉ ባለድርሻ አካላት ስልጠና ተሰጥቷል ያሉት ክቡር አቶ ሞቱማ በቀጣይ ወራትም ከመስክ ትግበራ የተገኘውን መልካም ተሞክሮ ለአጠቃቀም ምቹ በሆነ መልኩ በመሠነድ ለእቅድ ዝግጅትና ለፖሊሲ ግብዓት በሚሆን መልኩ ተቀናጅቶ ይቀርባል ብለዋል።
በአውደ ጥናቱ የፕሮጀክቱ አማካሪ ባለሙያዎች ባለፉት አስራ ሶስት ወራት ሲከናወኑ የነበሩትን ጥናቶች የተጠቃለለ የውሃ ሀብት አጠቃቀም ፣የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣቸው ተጽእኖዎች የመቋቋም አቅም ፣ የመልዕካ ምድርና የማህበረሰብ ተጋላጭነት አመላካች ጥናቶች እንዲሁም ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችሉ ተለይተው የተጠኑ የኢንቨስት መንት አማራጮችን የያዙ ሪፖርቶች ቀርበው የሚገመገሙበት ፣ በምክረ ሀሳቦች ዳብረው ለእቅድ ዝግጅትና ለፖሊሲ ግብዓት እንዲሆኑ የሚደረግበት አውደ ጥናት በመሆኑ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽአ እንዲያበረክት ክቡር አቶ ሞቱማ አደራ ብለዋል።
ለፕሮጀክቱ መሳካት ያልተቆጠበ ጥረት ያደረጉ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ማእከልና ኔትወርክ ፣ የውሃና ኢነርጂ እና የጄኔሬሽን የተቀናጀ የገጠር ልማት አማካሪ ድርጅት ባለሙያዎችን እና ሠራተኞችን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስም አመስግነዋል።
በአውደ ጥናቱ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ፣ከስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ቤዚን አስተዳደር ጽ/ቤት ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፣ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ፣ ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር ፣ ከኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲ፣ ከአዳማ ፣አዋሳ እና አሩሲ ዩኒቨርስቲዎች ፣ ከአለም ባንክ ፣ከግብርና ምርምር ማዕከል፣ ከውሃና መሬት ሀብት አስተዳደር ፣ ከማእከላዊ ኢትዮጵያ ግብርና ቢሮ፣ ከኦሮሚያ ክልል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ከ FAO እና wetland የተወከሉ እየተሳተፉ ነው።