" በመትከል ማንሰራራት"
የዛሬ ስድስት ዓመት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ አገራችን ለአለም ምርጥ ተሞክሮ ያበረከተችበት ነው ሲሉ አቶ ማሙሻ ሀይሉ ገለጹ።
ሀምሌ 24/2017ዓ.ም(ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ማሙሻ ሀይሉ የተመራ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና ተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች በኦሮሚያ ክልል ገላን አራብሳ ወረዳ በንስላሌ ቀበሌ ተገኝተው በአንድ ጀምበር 700ሚሊየን ችግኞችን የመትከል ዘመቻን እውን አድርገዋል።
አቶ ማሙሻ ሀይሉ የዛሬ ሰድስት ዓመት የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ከተጠቃሚነታችን ባሻገር ለአለም ምርጥ ተሞክሮ ያበረከትንበት ነው ብለዋል።
እስካሁን በነበረው የንቅናቄ ጉዞም የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብና በመጠበቅ በተሠራው ጠንካራ ስራ ከ85በመቶ በላይ ችግኞች መጽደቃቸው ለአበርክቶአችን ማሳያ ነው ብለዋል።
በዛሬው እለትም ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ፣ ከተጠሪ ተቋማት ፣ ከግብርና ሚኒስቴር እና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በንቅናቄ ከ10 ሺ በላይ ችግኞች መተከላቸውን አቶ ማሙሻ ገልጸዋል።
ችግኞችን ስንተክል ትውልድን የማስቀጠል ተግባርን አውን እያደረግን ነው ያሉት ኃላፊው የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ፣ ግድቦቻችን በደለል እንዳይሞሉ እና ዘላቂ ተጠቃሚነትን እንዲሰጡ ፣ የሀይል አቅርቦታችን የተሻለ እንዲሆን እንዲሁም ህይወት የሆነው የውሃ አካላታችን ደህንነት ተጠብቆ ተጠቃሚነታችን እንዲረጋገጥ ለመጭው ትውልድ የተሻለች ኢትዮጵያን የማስረከብ ትልቅ ንቅናቄ ነው ብለዋል።
ዛሬ የተተከሉ ችግኞችን እስከዛሬ ሲደረግ እንደነበረው በመንከባከብና በመጠበቅ ጥቅም ላይ እንዲውል የአካባቢው ማህበረሰብም ሆነ የተቋማት ግዴታም ሀላፊነትም ነው ብለዋል።
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባለሙያ የሆኑት ወ/ሮ ሊሻን ዮናስ ለአራተኛ ጊዜ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ መሳተፋቸው እንዳስደሰታቸውና እንደመንግስትም በዚህ ልክ ትኩረት ተሰጥቶ እየተደረገ ያለው ንቅናቄ በእጅጉ የሚመሠገን መሆኑን ገልጸውልናል።
የእንስላሌ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ወንዱ ለማ መሬቱ እተሸረሸረ አፈሩ በውሃ እንዳወሰድ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ በርካታ ችግኞች በመተከላቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው የተተከሉትን ችግኞች በመንከባከብና በመጠበቅ እንዲጸድቁ ቁርጠኛ ሆነው እንደሚሰሩና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።