የጎርፍ ስጋትነትን በመቅረፍ ወደ እድል የመቀየር ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተጠቆመ፡፡
ሀምሌ 23/2017 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ) በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር በክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ የተመራ የአመራሮች ቡድን በመካከለኛውና በታችኛው አዋሽ እየተከናወኑ የሚገኙ የጎርፍ መከላከል ስራዎችን የመስክ ምልከታ አድርገዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትሩ በመስክ ምልከታው ወቅት ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ የጎርፍ ስጋትነትን በመቅረፍ ወደ እድል የመቀየር ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል፡፡
ወንዙ በአግባቡ ባለመመራቱ በወንዙ ግራና ቀኝ የሚገኙ የእርሻ ቦታዎች ጥቅም እየሰጡ አልነበረም ያሉት ክቡር ሚኒስትሩ፤ የወንዝ ጠረጋ፣ የቦይ ማስፋትና የዳይክ ስራዎች በመሰራታቸው በግርፍ የተያዙ ሰፋፊ መሬቶች ወደ ልማት መግባታቸውን ገልጸዋል፡፡
በጎርፍ መከላከል ስራው 32 ሽህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ለመስኖ ልማት እንዲውል ያስችላም ብለዋል፡፡
የጎርፍ መከላከል ስራው 96 ኪ.ሜ. የሚሸፍን የወንዝ ጠረጋ፣ የቦይ ማስፋትና የዳይክ ስራዎችን እንደሚያካትት ጠቁመዋል፡፡
በአዋሽ ተፋሰስ በሚከናወን ሁሉንአቀፍ ጥናት መሰረት በማድረግ በቀጣይ ግድቦችንና የመሳሰሉ መሰረተልማቶችን በመገንባት አዋሽ ወንዝ በክረምት ጎርፍ እንዳያስከትል፤ በበጋ ደግሞ ውሃ እጥረትን ለመካላከል እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
የአፋር ብሔራዊ ክልል የመስኖና ተፋሰስ ቢሮ ሀላፊ አቶ ወላኣ ዊቲካ በተቀናጀ አግባብ ስራው መሬት በመውረዱ እና በመመራቱ ዉጤታማ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ተመስገን ከተማ በበኩላቸው ዘላቂ መፍሄ ለማምጣት ወደ ጥናት መገባቱን አንስተው፤ እየተከናወኑ የሚገኙ የጎርፍ መከላከል ስራዎች የጎርፍ ስጋትን የሚቀርፉ ናቸው ብለዋል፡፡