የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በአዋሽ ቤዚን አጠቃላይ ተፋሰሱን ያካተተ ጥናት ለማድረግ ከአለምአቀፍ አማካሪ ድርጅት ጋር ተፈራረመ፡፡
ሀምሌ 10/11/2017 (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ ጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት፤ በአዋሽ ተፋሰስ በዘላቂነት የጎርፍ አደጋ ስጋትን ለማስቀረት አጠቃላይ ተፋሰሱን ያካተተ ጥናት ለማድረግ ከኒኮላስ ኦደዉየር አማካሪ ድርጅት ጋር የውል ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ባለፉት አመታት የጎርፍ አደጋ በተደጋጋሚ በአዋሽ፤ በስምጥ ሸለቆ እና በኦሞ ጊቤ ተፋሰሶች መከሰቱን አንስተው፤ የጎርፍ ስጋትን ወደ እድል ለመቀየር የኢትዮጵያ የጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ ስራ መግባቱን ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ የጎርፍ መከላከል ፕሮጀክት የአስቸኳይና የዘላቂ ጎርፍ መከላከል ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ አውስተው፤ በላፈው አመት በአስቸኳይ ቅድመ ጎርፍ መከላከል ስራዎች በላይኛው፣ በመካከለኛውና በታችኛው አዋሽ ተፋሰሰ የዳይክ ስራዎችን በማከናወን፤ የወንዝ ማስፋት ስራዎችን በመስራትና የደለል ማውጣት ስራዎችን በማከናወን 151.1 ኪ.ሜ የወንዝ ዳር ጎርፍ መከላከያ የግንባታ ስራች በማከናወን ከ 48 ሽህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎች እና 28 ሽህ በላይ ሄክታር የእርሻ መሬት ከጎርፍ አደጋ መጠበቅ ተችሏል ብለዋል፡፡
በዚህ አመትም በአዋሽ ተፋሰስ፣ በስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ተፋሰስ እና በኦሞ ጊቤ ተፋሰስ ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የአስቸኳይ የቅድመጎርፍ መከላከል ስራዎች እተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የጎርፍ አደጋን በዘላቂነት ለመከላከል የኒኮላስ ኦደዉየር አማካሪ ድርጅት በአንድ አመት ውስጥ አጠናቆ በሚያመጣው የጥናት ዉጤት ላይ በመመስረት የምህንድስና ስራዎች እንደሚተገበሩ ተናግረዋል፡፡
በመካከኛው አዋሽ ላይ አነስተኛ ግድቦች፣ የውሃ መጥለፊያ ወይም የውሃ ማጠራቀሚያ መሰረተልማቶች እንደሚገነቡ ገልጸዋል፡፡
ተመሳሳይ ጥናቶችን በስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ተፋሰስና በኦሞ ጊቤ ተፋሰስ ላይ ለማከናወን በጨረታ ሂደት ላይ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡
የኒኮላስ ኦደዉየር አማካሪ ድርጅት ዋና ስራ አአስኪያጅ ሚ/ር ኒኮላስ ኦደዉየር በበኩላቸው ድርጅታቸው ያለውን የጎርፍ አደጋ ስጋት እንደሚረዳ ገልጸው፤ የጎርፍ አደጋ ስጋቱን መቀልበስ የሚያችል መፍትሄ ይዘው እመንደሚመጡ ገልጸዋል፡፡