ክቡር ሚኒስትሩ የአለምአቀፉ የሚቲዮሮሎጂ ድርጅት ዋና ጸሃፊን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ፡፡
ሀምሌ 9/2017 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ከአለምአቀፉ የሚቲዮሮሎጂ ድርጅት ዋና ጸሃፊ ፕሮፌሰር ሰለስቴ ሳዉሎ ጋር ተወያዩ፡፡
ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በኢትዮጵያ የሚቲዮሮሎጂ አገልግሎት ለግብርና፣ የጤና የውሃ ሀብት አስተዳደርና ሌሎች ዘርፎችን በብቃት እየደገፈ መሆኑን ጠቅሰው፤ የአየር ጸባይ ትንበያ ስራው አስተማማኝነትና ትክክለኛነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትሩ አክለውም በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ባለፉት አመታት ከ40 ቢሊየን ችግኞች በላይ በመትከል የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ተደርጓል ብለዋል፡፡
ንጹህ ታዳሽ ኢነርጂ ለቀጠናው ሀገራት በማቅርብም በቀጠናው የካርቦን ልቀት መጠን ቅነሳ ላይ አስተዋጽኦ እያበረከትን ነው ብለዋል፡፡
የአለምአቀፉ የሚቲዮሮሎጂ ድርጅት ዋና ጸሃፊ ፕሮፌሰር ሰለስቴ ሳዉሎ በኢትዮጵያ የሚቲዮሮሎጂ አገልግሎት ያለበት ደረጃ የሚደነቅ መሆኑን አንስተው፤ የአለም ሜቲዮሮሎጂ የአፍሪካ አህጉር ጽ/ቤት በኢትዮጵያ መገኘቱ በአመራር በኩል ያለውን ጥንካሬ ያሳያል ብለዋል፡፡
ዋና ጸሃፊዋ የሚቲዮሮሎጂ አገልግሎትን ለማዘመን አለምአቀፉ የሚቲዮሮሎጂ ድርጅት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናረግዋል፡፡