ፕሮጀክቱን ተመረቀ ብሎ ችላ ማለት ሳይሆን ሀላፊነት ወስዶ መጠበቅና መንከባከብ ከህብረተሰቡ እንደሚጠበቅ ተገለጸ።

ፕሮጀክቱን ተመረቀ ብሎ ችላ ማለት ሳይሆን ሀላፊነት ወስዶ መጠበቅና መንከባከብ ከህብረተሰቡ እንደሚጠበቅ ተገለጸ። ሀምሌ/2017 (ው.ኢ.ሚ) የውሀና ኢነርጅ ሚኒስቴር በጎፋ ዞን ሳውላ ከተማ በውሃ ልማት ፈንድ ያስገነባው የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክትን ተመረቀ ብሎ ችላ ማለት ሳይሆን ሀላፊነት ወስዶ መጠበቅና መንከባከብ ከህብረተሰቡ እንደሚጠበቅ የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ ። የሳውላ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሊበን ጉሌ እንደገለጹት ከዚህ ቀደም የነበረው የውሃ አቅርቦት አነስተኛና በሳምንት ሁለት ቀን ብቻ በመሆኑ ከወንዝ መቅዳት ይገደዱ እንደነበር ገልጸው፤ በዚህ ፕሮጀክት ያን ችግር የሚቀርፍ ፕሮጀክት ለአገልግሎት መብቃቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል። አቶ ሊበን በማከል ፕሮጀክቱን ተመረቀ ብሎ ችላ ማለት ሳይሆን ሀላፊነት ወስዶ መጠበቅና መንከባከብ ይጠበቅብናል ብለዋል። ፕሮጀክቱ በተለይ ለሴቶች ከፍተኛ ጫናን የሚቀንስም ነው ብለዋል። ከዚህ በፊት የነበረብንን ችግር አይቶ ለከተማዋ ልማት እና ህብረተሰብ የሚጠቅምና ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የጤና ችግርን የሚፈታ ፕሮጀክት እንዲተገበር ላደረገው የፌደራልና የክልሉ መንግስት፤ እንዲሁም በፕሮጀክቱ ትግበራ የተሳተፉትን አካላት ሁሉ አመስግነዋል። ሌላኛዋ የከተማው የንጹህ መጠጥ ውሀ ተጠቃሚ የሆኑት ወ/ሮ ከበቡሽ ክፍሌ በፕሮጀክቱ የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ በከተማዋ የነበረው ውሃ ረጂም ጊዜ ያገለገለና አሁን ላይ የተጠቃሚው ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ፤ የውሃ መስመሮች ብልሽት ምክንያት ውሃ የሚያገኙት በፈረቃ በመሆኑ እስከ ዛሬ ከፍተኛ የሆነ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር የነበረባቸው መሆኑን ገልጸዋል። ወ/ሮ ከበቡሽ በማከል ፕሮጀክቱ በከተማዋ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚሰጥና የተለያዩ የልማት ስራዎች እንዲተገበሩ የከተማዋ እድገት እንዲፋጠን ከፍተኛ አስተዋጾ እንዳለው ገልጸዋል፡፡ ፕሮጀክቱ በአግባቡ ለሁሉም ህብረተሰብ መዳረስ እንዲችልና በዘላቂነት ችግራቸውን እንዲፈታ፤ ችግኞችን በመትከል የአካባቢ ጥበቃ ስራን በትብብር በመስራት፤ ውሃውን በፍትሀዊነት መጠቀም፤ የከተማው ውሃ አገልግሎት ከህብረተሰቡ ጋራ መስራት አለበት በማለት አስተያየትም ሰጥተዋል።

Share this Post