የሻንቶ ከተማ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

የሻንቶ ከተማ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።

ሀምሌ5/2017 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በባስኬት ፈንድ ፕሮጀክት በውሃ ልማት ፈንድ አስተባባሪነት ወላይታ ዞን ሻንቶ ከተማ በ208 ሚሊየን ብር ወጭ ያስገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ በይፋ ስራ መጀመሩን በስፍራው ተገኝተው ያበሰሩት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ጥላሁን ከበደ የከተማዋን ህዝብ የዘመናት የንጹህ መጠጥ ውሃ ፍላጎት ጥያቄ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ተቀብሎ ፕሮጀክቱን ገንብቶ ስላቀረበልን እናመሠግናለን ብለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በማከል ከለውጡ ማግስት በክልላችን በርካታ ትላልቅ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ እንደሚገኙ ጠቁመው የሻንቶ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክትም የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል።

የሻንቶ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት ከ29 ሺ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን የመጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸው በፕሮጀክቱ በዘላቂነት ለመጠቀም የአካባቢው ህብረተሰብ የክፍያ ስርዓቱን ተከትለው የአገልግሎት ክፍያቸውን በመክፈል መጠቀም እንዳለባቸው እንዲሁም የውሃ ሀብቱን በዘላቂነት ለመጠቀም ችግኞችን በመትከል በመንከባከብና በመጠበቅ የአረንጓዴ ፕሮጀክቶቹን ዘላቂነት ማረጋገጥ የሁሉም ሀላፊነት መሆኑን አሳስበዋል።

በመጨረሻም ለዚህ ፕሮጀክ መሣካት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል።

በምርቃት ስነስርአቱ ላይ የተገኙት የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ትልቅ መዋእለ ንዋይ ፈሶበት በብድር የተገነባውን ፕሮጀክት በብድር አመላለስ ስርዓቱ መሠረት ተመላሽ ማድረግ ሌሎች ይህንን እድል ያላገኙትን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል ብለዋል።

ክቡር ሚኒስትሩ በማከል የሻንቶ ከተማን የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት አጠናቀን ለአገልግሎት ስናበቃ ለህብረተሰቡ በፍትሀዊነት የውሃ ክፍፍል ማድረግ ደግሞ ከውሃ አገልግሎት ይጠበቃል ብለዋል።

ህብረተሰቡም የአገልግሎት ክፍያውን በአግባቡ በመክፈል ሌሎች ፕሮጀክቶችን መገንባት እንደሚቻል አክለው ገልጸዋል ።

በመጨረሻም ክቡር ሚኒስትሩ ህብረተሰቡ ክፍያውን በአግባቡ በመክፈል ፣ ፕሮጀክቱን በመንከባከብ ፣ብክነትን በመቀነስ መጠቀም ከቻለ ተጨማሪ ፕሮጀክት መስራት ይቻላል በማለት አሳስበዋል።

በክልሉ ሌሎች ፕሮጀክቶችም በቅርቡ እንደሚጠናቀቁ ተገልጿል።

ፕሮጀክቱን ለተገበሩ አመራሮች፣ ባለሙያዎች ፣ ኮንትራክተሮች፣አማካሪዎች እና ለክልሉ መንግስትና ለህብረተሰቡ ክቡር ሚኒስትሩ ምስጋና አቅርበዋል።

በእለቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም ተከናውኗል።

በመርሀ ግብሩ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትርን ጨምሮ የበላይ አመራሮች የሀገር ሽማግሌዎች ኮንትራክተሮችና የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል።

Share this Post