የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የሃይድሮሎጂ ኡደትን በማስተካከል በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተጠቆመ፡፡
የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የሃይድሮሎጂ ኡደትን በማስተካከል በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ተጠቆመ፡፡
ሀምሌ 04/2017 ዓ.ም. (ው.ኢ.ሚ) በኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢስቲቲዩት ግቢ ውስጥ በተካሄደው የዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ ማስጀመሪያ መርሃግብር ላይ የተገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሡልጣን ወሊ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር የሃይደሮሎጂ ኡደትን በማስተካከል በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡
ዝናብ ወቀቱን ጠብቆ እንዲዘንብ ከማድረግ ባሻገር የውሃ ስርገት መጠንን በመጨመር የከርሰምድር ውሃ ሃብታችን እንዲበለጽግ ያስችላልም ብለዋል፡፡
ግድቦቻችንና ሀይቆቻችን በደለል እንዳይሞሉ በማድረግ የታለመላቸውን አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላልም ሲሉ ተናግረዋል።
ባለፉት አመታት ከ40 ቢሊየን በላይ ዘርፈብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መተከላቸውን የገለጹት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው የአፈር መሸርሸርን በመከላከልና በመቀነስ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናችንን እንድናረጋግጥ ያስችላል ብለዋል፡፡
ለም አፈር ታጥቦና ተሸርሽሮ እንዳይሄድ በማድረግ ለማዳበሪያ የሚወጣውን ወጪ የመቀነስ አቅም እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው የአረንጓዴ አሻራ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለማብሰያነት የዋሉ ባዮማሶችን መልሶ ለመተካትና የስራ እድል በመፍጠር ሂደት ላይ ያለውን ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ጠቁመዋል፡፡
በማስጀመሪያ መርሃግብሩ ላይ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እና የተጠሪ ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች ተሳትፈዋል፡፡