የባዘርኔት ፕሮጀክትን አተገባበር ላይ የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው።

የባዘርኔት ፕሮጀክትን አተገባበር ላይ የአቅም ግንባታ ስልጠና እየተሰጠ ነው። ሰኔ 17/2017 ዓ/ም( ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የባዘርኔት ፕሮጀክትን በሙሉ አቅሙ ወደ ትግበራ ለማስገባት የሚያግዝ በፕሮጀክት ማኔጅመንት ላይ ያተኮረ የአቅም ግንባታ ስልጠና ለዘርፉ አመራሮች በአዳማ እየተሰጠ ነው። በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የባዘርኔት ፕሮጀክት ብሔራዊ አሰስተባባሪ አቶ ሞላ ረዳ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በርካታ ፕሮጀክቶችን የሚያስገነባና የሚተገብር በመሆኑ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችንም ሆነ አመራሮችን የፕሮጀክት አስተዳደር ዕውቀት ለማስጨበጥ እና ለተግባራዊነቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ስልጠና ተዘጋጅቷል ብለዋል። ፕሮጀክቱ በጣሊያን መንግሥት እንደሚደገፍና የአዋሽና ዋቢ ሸበሌ ተፋሰሶች መረጃ አያያዝን ማዘመን፣ለአርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር በቂ የውሃ አቅርቦትን ማረጋገጥ፣የተፋሰሶች እንክብካቤና የወንዞች ዳርቻ ልማት፣ለዘርፉ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች አቅም የመገንባት ስራና በሁለቱ ተፋሰሶች ላይ ለሚሰራው የልማት ስራ የሶላር ኢነርጅ ተደራሽ ማድረግ የሚሉ 5 ክፍሎች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ ገልጸው ለፕሮጀክቱ ውጤታማት ስልጠናው ወሳኝ እንደሆነም አክለዋል። በስልጠናው የሁለቱ ተፋሰሶች መገኛ ከሆኑት የኦሮሚያ፣ የአፋርና የሶማሌ ክልል የውሃ ሴክተር ሀላፊዎችና የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የዘርፉ ሀላፊዎች እየተሳተፉ የይገኛል። ስልጠናው ለ5 ተከታታይ ቀናት እንደሚሰጥም ማወቅ ተችሏል።

Share this Post