የንጹህ ማብሰያ ፍኖተ ካርታው የምግብ ማብሰል ሂደቱን ጤናማ ከማድረግ ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ተገለጸ፡፡
ሰኔ 17/2017ዓም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የንጹህ ማብሰያ ፍኖተ ካርታው የምግብ ማብሰል ሂደቱን ጤናማ ከማድረግ ባለፈ በጤና፣ በጾታ እኩልነት፣ በትምህርት፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በደን እና በሰዎች ኑሮ ላይ የሚያመጣው ለውጥ በርካታ መሆኑ ተገለጸ፡፡
በመርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኢ/ር ሡልጣን ወሊ ፍኖተ ካርታው የሥርዓተ-ፆታ እኩልነትን ያካተተ በመሆኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶችን በንፁህ የምግብ አሰራር የእሴት ሰንሰለት ለማብቃት ያለመና በሴቶች ለሚመሩ ኢንተርፕራይዞችም በአቅርቦት ሰንሰለት፣ ስርጭት እና አገልግሎት ላይ ትልቅ ሚና እንዳው ገልጸዋል።
በሀገራችን ከ100 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን በዋነኛነት ሴቶች እና ህጻናት አሁንም በባህላዊ ባዮማስን እንደ ማገዶ፣ ከሰል እና የከብቶች እበትን ላይ ጥገኛ መሆናቸውን ገልጸው ይህም የጤና ቀውስ ከማስከተሉ ባሻገር በየአመቱ ከ63 ሺ በላይ ዜጎችን ያለጊዜያቸው ለሞት እንዲዳረጉ አስተዋፅዖ ያደርጋል ብለዋል፡፡
ክቡር ሚኒስተር ዲኤታው በዋናነት ፍኖተ ካርታው ከ90 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ንፁህ የማብሰያ ቴክሎጅዎችን እንዲያገኙ እንደሚየያደርግ፣ 36 ሚሊዮን እርከን 3 እና ከዚያ በላይ ማብሰያ ምድጃዎችን ለማሰማራጨት፣ 75 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ካርበንዳይኦክሳይድ ተመጣጣኝ ልቀት መቀነሱ፣ ከ335,000 በላይ ምድጃዎችን በማምረት፣ ለማከፋፈል ይሰራል ብለዋል፡፡
ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ለሴቶች የሚያስፈልገው አጠቃላይ ኢንቨስትመንት 3.38 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሲሆን፤ የቴክኖሎጂ ግዥን ጨምሮ የህብረተሰቡን የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻዎችን የሚያጠቃልል መሆኑንና ፍኖተ ካርታው እስከ 2035 ተግባራዊ ይሆናል ብለዋል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሚንስትር ዲኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤልያስ ከዚህ በፊት በሀገራችን የንጹህ ማብሰያ ቴክኖሎጂ ባለመኖሩ አካባቢያችን ከመራቆት አልፎ ለአፈር መሸርሸር በመዳረግ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በመቀነስ ለአየር ንብረት መዛባትና ሌሎች ተዛማጅ ችግሮች እየተጋለጥን ነበር አሁን ላይ የንጹህ ማብሰያ ቴክኖሎጂው የአፈር ለምነትን በማስጠበቅ ለግብርና ምርታማነት እና ለኤክስቴንሽን ተሻሽሎ የቀረበው ማብሰያ ስርዓት ፍኖተ ካርታው እንደ ግብርና ሚኒስቴር ትልቅ ቴክኖሎጂ ተደርጎ እንደሚወሰድ እና የአረንጓዴ አሻራን የሚያጠናክርና አጋዥም ይሆናል ብለዋል፡፡
በመርሀ ግሩ ላይ በጤና ሚኒስቴር ሚኒስተር ዴኤታ፣ ፣ በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማት ሚንስትር ዲኤታ ፣ በከተማ ፕላን ልማት፣ በትምህርት፣ አጋሮች የግል ሴክተሮች እና ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት የንጹህ ማብሰያ ፍኖተ ካርታው ይፋ ተደርጓል፡፡