የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግርን በመፍታት ሀገራችን ለወር አበባ ንፅህና አጠባበቅ ተደራሽ እንድትሆን መስራት ይገባል ተባለ።
ሰኔ /2017 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከጤና ሚኒስቴር ጋር በጋራ በመሆን በአለም አቀፍ ደረጃ ለ12ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ለ9ኛ ጊዜ "ለወር አበባ ንፅህና ተደራሽ የሆነ ሀገርን በጋራ እናረጋግጥ!" በሚል መሪ ቃል የሚከበረው የወር አበባ ጤናና ንፅህና አጠባበቅ አመታዊ ክብር በዓል ላይ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግርን በመፍታት ሀገራችን ለወር አበባ ንፅህና አጠባበቅ ተደራሽ እንድትሆን መስራት ይገባል ተባለ።
በመድረኩ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርን ወክለው የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የብሔራዊ ዋን ዋሽ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ አብይ ግርማ ሴቶችና ልጃገረዶች የወር አበባ ንፅህናቸውን ለመጠበቅ ያለንፁህ ውሃ አቅርቦት የሚታሰብ ባለመሆኑ እንደ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባለፉት አስርት ዓመታት የንፁህ ውሃ አቅርቦትና የመፀዳጃ ቤት ግንባታን ተደራሽ ከማድረግ አንፃር ትልቅ መሻሻል ቢታይም አሁንም ለበርካታ ነዋሪዎች በስታንዳርዱ መሰረት የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እና የመፀዳጃ ቤት ሙሉ በሙሉ ተደራሽ ስላልሆነ በቀጣይ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
አቶ አብይ አያይዘውም የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግርን በመፍታት ሀገራችን ኢትዮጵያ ለወር አበባ ንፅህና አጠባበቅ ተደራሽ የሆነች ሀገር እንድትሆን መስራት የሚጠበቅብን በመሆኑ ሚኒስቴር መ/ቤታችን በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት ለዘርፈ ብዙ ጥቅም የሚውለውን የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ስራዎችን የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራና በቅንጅት እንደሚሰራ ቃል እንገባለን ብለዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴርን ወክለው መድረኩን በይፋ የከፈቱት የማህበረሰብ ተሳትፎና የመጀመሪያ ደረጃ ጥናት እንክብካቤ መሪ ስራ አስፈፃሚ አቶ እስራኤል አታሮ በወር አበባ ጤናና ንፅህና አጠባበቅ ዙርያ በሴቶችና ልጃገረዶች ላይ የሚደርሰውን መገለል ብሎም የንፅህና መጠበቂያ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ አለማግኘት፤ ተማሪዎች ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስ ከሚመለከታቸው ባለድርሻዎች ጋር በጋራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
አቶ እስራኤል አክለውም መንግስት የችግሩን አሳሳቢነት በጥልቀት በመረዳት በሴቶች የንፅህና በ2012 ዓ.ም ተጥሎ የነበረውን 30% ታክስ ወደ 10% በማውረድ ከፍተኛ ሚና እንዲኖረው አስታውሰው፤ ችግሩ አሁንም አሳሳቢ በመሆኑ ሴቶች በወር አበባቸው ወቅት የወር አበባ ንፅህና መጠበቂያ መግዛት አቅም ውስንነት ላይ ልጃገረድ ተማሪዎችና ሌሎችም በየወሩ ገዝተው መጠቀም ለማይችሉት መንግስት የችግሩን ከፍታና አሳሳቢነት በመረዳት በሴቶች የንፅህና መጠበቂያ ላይ ከታክስ ነፃ (ዜሮ %) በማድረግ ለችግሩ መፍትሄ እንደሚሰጥ እናምናለን ብለዋል፡፡
የመድረኩም ዋና ዓላማ 50% ለሚሆኑ የሀገራችን ሴቶች የወር አበባ ንፅህናቸውን ለመጠበቅ ከታክስ ነፃ የሆነ የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች፣ የንፁህ ውሃ አቅርቦትና ለሴቶች ምቹ የሆኑ መፀዳጃ ቤቶችን ለመገንባት ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ለማስገንዘብ ነው።
በመድረኩ በኢትዮጵያ የዩኒሴፍ ተወካይ Ms. Mariko Kagoshimaን ጨምሮ ከውሃና ኢነርጂ፣ ከጤና፣ ከትምህርትና ከገንዘብ ሚኒስቴር ተወካዮች፣ ከመንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ የልማት አጋር ድርጅቶች፣ የሲቪል ማህበራት ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የታደሙ ሲሆን፤ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡