አደሌ አና ኢሊፕ ፕሮጀክቶች የህብረተሰቡን የሀይል ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሚናቸው የላቀ ነው ተባለ።
ሰኔ /2017 ዓ.ም (ው.ኢ.ሚ) Access to Distributed Electricity and Lighting in Ethiopia (ADELE) እና Ethiopian Electrification program (ELEAP) ፕሮጀክቶች ከዋናው የሀይል መስመር ርቀው የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሀይል ተጠቃሚ ለማድረግ ሚናቸው ከፍተኛ መሆኑን ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሱልጣን ወሊ ገልጸዋል።
በድሬዳዋ ከተማ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ በቆየው የውይይት መድረክ ላይ የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሡልጣን ወሊ ከዋናው የሀይል መስመር ርቀው የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎችን በአደሌ አና ኢሊፕ ፕሮጀክቶች የሀይል ተጠቃሚ ለማድርግ በርካታ ስራዎች መሠራታቸውን አብራርተዋል።
በዘርፉ የተከናወኑ ተግባራት ለሌሎች ሀገራት ተሞከሮ የሚሆኑ ናቸው ያሉት ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው በፕሮጀክቱ 4 ሶላር ሚኒግሪዶችን ለመትከል ታቅዶ 11 ሶላር ሚኒግሪዶችን በመትከል ውጤታማ ስራ ሰርተናል ብለዋል።
በውይይቱ ለተነሱት ጥያቄዎች ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በቀጣይ ሁሉም በተሰማራበት መስክ የፕሮጀክቱን ዓላማ ለማሳካት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም አሳስበዋል።
በምስራቅ ሀረርጌ ዞን የውሃና ኢነርጂ ቢሮ የኢነርጂ ሀብት ልማት ቡድን መሪ አቶ ኢብራሂም አብዲ የሶላር ኢነርጂ በዞናቸው ውጤታማ ከመሆኑም በላይ በ21 ወረዳዎች የሚኖሩትን አርሶአደሮች፣ ት/ት ቤቶችንና የጤና ኬላዎችን ተደራሽ ለማድረግ በተሰሩ ስራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ገልፀዋል።
በሀረሪ ክልል የኤረር ወረዳ ም/አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል በበኩላቸው የሶላር ኢነርጂን በግለሰብም ሆነ በተቋም ደረጃ መጠቀምን ልምድ በማስፋት፣ የከርሰምድር ውሃን በመሳብና ለመስኖ በመጠም የነዳጅ ወጪ መቀነሳቸውን ገልፀው፤ ተቋሙ ለሚያደርግላቸው ክትትልና ድጋፍም አመስግነዋል።