የአዴሌ ፕሮጀክት ትግበራ፣ መመሪያና በአካባቢ ጥበቃ አስተዳደር ስርአት ዙሪያ ከሚመለከታችው ባለድርሻዎች ጋር ውይይት እየተካሄደ ነው።
ሰኔ 08/2017 ዓ/ም (ው.ኢ.ሚ) የውሃና ኢነርጂ ሚንስቴር በብሔራዊ የኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም የአዴሌ ፕሮጀክት (Access to Distributed Electricity and Lighting in Ethiopia) ትግበራ፣ መመሪያና በአካባቢ ጥበቃ አስተዳደር ስርዓት ዙሪያ ከክሎች እና ዞኖች ከተውጣጡ ባለድርሻዎች ጋር ውይይት እየተካሄደ ነው።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሡልጣን ወሊ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የብሔራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራም ትግበራን የመምራትና የማስተባበር ሃላፊነትን በሚገባ እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ከአለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በኢሊፕ ፕሮግራም ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ተጠቃሚዎችን የማገናኘት ስራ እና በአደሌ ፕሮጀክት ደግሞ በጣም ገጠራማ ለሆኑና ከዋናው የሀይል መስመር ርቀው የሚገኙትን ማህበረሰብ በሶላር ሀይል ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ ለቤተሰብ፣ ለማህበራዊ ተቋማትና ለንግድ ድርጅቶች አስተማማኝ የሀይል አቅርቦት ተደራሽነትን ማስፋፋት ነው ያሉት ከቡር ሚኒስትር ዴታው በአደሌ ፕሮጀክት በአዲስ አበባና በተመረጡ 10 ከተሞች 938 ኪ.ሜ የመካከለኛ ሀይል የማሰራጨት ፣ የማሻሻልና የማስፋፋት ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
ክቡር ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም ፕሮጀክቱ በክልሎች የሚተገበር በመሆኑ በተዘጋጁ ሰነዶች ላይ የክልል፣ የዞንና የወረዳ ቢሮ ኃላፊዎችና ተወካዮች በፕሮጀክቱ አተገባበር፡ ስለብሔራዊ ኤሌክትሪፊኬሽን ፕሮግራምና ስለአደሌ ፕሮጀክት ግንዛቤ ለማስጨበጥ ፣ በሶላር ሆም ሲስተም የተዘጋጀውን የአካባቢና ማህበራዊ አስተዳደር መተግበሪያ ሰነድ ላይ የጋራ ግንዛቤ አንዲኖር የሚያስችል ውይይት ነውም ብለዋል።
ስልጠናው ከዚህ በፊት በሃዋሳና በጅማ ከተማ ለኦሮሚያ፣ ለደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ ለደቡብ ኢትዮጵያ፣ ለማዕከላዊ ኢትዮጵያና ለሲዳማ ክልል የኢነርጂ ቢሮ ኃላፊዎችና ተወካዮች የተሰጠ መሆኑንም አስታውሰዋል።
የድሬዳዋ ከተማ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ፉአድ መሀመድ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በዘርፉ የሀይል ተደራሽነትን ለማስፋፋት አያከናወነ ያለው ተግባር ከቀናት በፊት በተቋሙ ግቢ ውስጥ ያስመረቀው የሶላር ኃይል ማመንጫ ፐሮጀክት ማሳያ ነው ብለዋል።
በስልጠናው ላይ ከክልሎች ከዞኖችና ከወረዳ የኢነርጂ ቢሮ ባለሙያዎችና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ሲሆን ውይይቱ ለቀጣይ ሁለት ቀናት ይሰጣል።